ቀጥታ፡

ለአገራዊ ለውጡ እፎይታ የሰጡ ተግባራት

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 27/2012 ለአገራዊ ለውጡ እፎይታ የሰጡ ተግባራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ከትላንት በስቲያ ባካሔዱት 1ኛ ልዩ ስብሰባና ላይ ተገኝተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ ማብራሪያና ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የነበሩ የለውጡን ፈተናዎች አስመልክተው ለምክር ቤቱ አባላት ለትውስታ ገለጻ አድርገዋል። ዶክተር ዐብይ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ወደፊት አለመጓዝ ብቻ ሳይሆን ባለችበት መቆም የሚያቅታት ወቅት ላይ ደርሳ ነበር። በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች አገሪቱን ለማስቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሶም እንደነበረ ነው ያስታወሱት። ለእዚህም ለውጡን የተፈታተኑ ተግዳሮቶች በየአቅጣጫው ተከስተው እንደነበር የተወሰኑትን በዋቢነት በመጥቀስ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል። ቀድሞ በነበረው መንግስት የነበሩ ውስብስብና ጥልፍልፍ ትስስሮች እንዲሁም ያልተገቡ ግንኙነቶች ሀገረ መንግስቱን በግለሰቦችና በተወሰኑ ቡድኖች እጅ እንዲወድቅ ከማድረግ ባለፈ ለአገራዊ ለውጡ ተግዳሮት እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። ይህን ጥልፍልፍ፣ ውስብስብና በውል ያልተለየ ግንኙነት ከስር መሰረቱ በጣጥሶ ትክክለኛ ስርአት መገንባት ለለውጡ አካል ቀላል ተግባር አልነበረም። “ከዚህ ባሻግር ያንን ውስብስብና የተሳሰር ግንኙነት መገንዘብ በራሱ ውሱንነት ነበረው” ሲሉ ነው የገለጹት። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተግዳሮት ሆኖ የነበረው ይህ ቀጥተኛ ያልሆነ እና ያልተገባ ግንኙነት በጥቅም፣ በዘር፣ በዝምድና በጓደኝነት የተሳሰረ በመሆኑ ወዲያው ማጥፋት አልተቻለም። ከውስጡ አንዳንድ ገመድ በሂደት መለየትና መበጠስ ሲጀመር የትስስሩ ገመድ ተበጣጥሶ ያለቀና የቆመ የመሰላቸውም ነበሩ። ይህ ትስስርና ያልተገባ ግንኙነት እስከ ታችኛው አስፈፃሚ አካል ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ መሆኑን ካለመገንዘብ የተፈጠረ ስሕተት መሆኑን ነው ዶክተር ዐብይ ያመለከቱት። የተሳሰረው ግንኙነት በለውጡ ማግስት ሲፈልግ ነገሮችን የሚያስኬድ፤ ሲያሻው ደግሞ ማስቆም የሚያስችል ደረጃ ላይ ነበር። ዶክተር ዐብይ እንዳሉት በመጀመሪያዎቹ የለውጡ ወራት በፓለቲካ ምክንያት የታሰሩ ታራሚዎችን ለመፍታት ሲታሰብ የትስስሩ አካል መገዳደር የሚችል ቢሆንም ማስቆም ባለመቻሉ እቅዱን በተሳካ መልኩ በመፈፀም ታራሚዎችን ለመፍታት ተችሏል። ከእዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አገራት የታሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ማስፈታትና ብዙዎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ታቅዶ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል። ሥራው ቀላል ባይሆንም ማሳካት መቻሉንና ይህ የተደራጀ ኃይል ሊገታው ያልቻለ ዕቅድ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል የነበረውን ስርአት በመቃረን ታጥቀው በውጭ አገር ሲታገሉ የነበሩ አማጽያን ወደአገር ውስጥ ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የተደረገውን ጥሪና ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃም ፈታኝ ተግዳሮቶች እንደነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት አስታውሰዋል። በስደት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲካኞችም ወደአገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የነበረው ፈተና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ዶክተር አብይ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተወሰዱ የማስተካካያ እርምጃዎችንም ለምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል። ለአብነትም በተለያየ ምክንያት በግልጽ በሚታወቅ መንገድ ስርጭታቸው ወደህዝብ በአግባቡ እንዳይደርስ ከተደረጉት መገናኛ ብዙሀን ባሻገር በመቶ የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ አይነቶች እንዲዘጉ የተደረጉበት ሁኔታን ለውጡ በተጀመረበት ማግስት መቀየር መቻሉን ነው የጠቀሱት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰዎች በነፃነት ሀሳባቸውን ማራመድ እንዲችሉ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት በእዚሁ በውስብስብና ጥልፍልፍ ትስስሩ ሳይስተጓጎል መከወን እንደተቻለ አስታውሰዋል። በአገሪቱ የነበሩ አፋኝ ሕጎች ለዚህ ምክር ቤት ቀርበው ቢሻሻሉ ሥራዎችን ሊያቀላጥፉ እንደሚችሉ በመታመኑ ቀርበው እንዲሻሻሉ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ሂደቱ የራሱ የሆነ ፈታኝ ነገሮች የነበሩት ቢሆንም በተወሰኑ ቡድኖች እጅ የነበረው ትስስር ይህንን ለማስቆም የሚያስችል ብቃት እንዳልነበረው ነው ያስረዱት። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገለጻ እነዚህ ስራዎች ከተከናወኑ በኋላም የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት፣ በአዲስ መልክ ለማደራጀት እንዲሁም የተቋማቱንም ሆነ የአመራሩን አቅም ለማጠናከር እንዲቻል የተሔደበት ርቀት በራሱ በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩበት። ነገር ግን ቢያንስ ምርጫ ቦርድን በአደረጃጀት፣ በህግ፣ በአመራር ብቃት ስራውን መከወን በሚያስችል ደረጃ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የገጠሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን በሆነ መንገድ እፎይታ ሊሰጡ የሚችሉ ስራዎችን ለማከናወን መቻሉን ነው የገለጹት። ይህን ተከትሎም ተቋማት በሙሉ እግራቸው ቆመው መንቀሳቀስ እንዲችሉ በአሁኑ ወቅት ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም