ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የደረሱበትን የስምምነት ሰነድ እስከ የካቲት አጋማሽ ይፈራረማሉ

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 27/2012 ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አጠቃቀም ላይ የደረሱበትን የስምምነት ሰነድ እስከ መጪው የካቲት አጋማሽ እንደሚፈራረሙ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሦስቱ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል፣ የድርቅ ማካካሻና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ለአራት ቀን የፈጀ ድርድር ማድረጋቸው ይታወሳል። ዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ታዛቢዎች በሆኑበት በዚህ ድርድር ሦስቱ አገራት የነበራቸውን ልዩነት በማጥበብ ወደ ስምምነት እንደደረሱ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነርጂ ስለሺ በቀለ ተናግረዋል። ስምምነቱ በዋናነት አራት መሰረታዊ ሰነዶችን የያዘ ሲሆን እነሱም ጠቅላላ የህግ ማዕቀፍ፣ የቴክኒክ ጉዳዮች፣ የመረጃ ልውውጥና ሠላማዊ የግጭት አፈታትን የተመለከቱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ተዘጋጅቶ ያለቀው የቴክኒክ ጉዳዮች ረቂቅ ሰነድ ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ ከሦስቱም አገራት በተውጣጡ የህግ ባለሙያዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሦስቱ ሰነዶች ተዘጋጅተው ሳያልቁ የቴክኒክ ረቂቁን ሰነድ ኢትዮጵያ እንድትፈርም ግብፅ ጥያቄ አቅርባ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ "ሁሉም ሰነዶች በስምምነቱ መሰረት ተዘጋጅተው ሳይቀርቡ ኢትዮጵያ በተናጠል እንደማትፈርም አቋሟን አሳውቃለች" ብለዋል። በተለይ ለረዥምና ለአጭር ጊዜ በሚቆይ የድርቅ ሁኔታ እንዲሁም በትነትና በአጠቃቀም ውሃ ሲቀንስና ሲጨምር እንዴት ይለካል? እንዴትስ ይካካሳል? በሚለው ጉዳይ በአገራቱ መካከል ከፍተኛ ልዩነት የነበረበት መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ልዩነቱን በማጥበብ መስማማት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። "ስምምነቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ለመሙላት በሚያስችላት የግንባታ ደረጃ ላይ ስትደርስ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ማጠራቀም ሥራ መጀመር እንድትችልና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለቱን ተርባይኖች በመጠቀም ኃይል እንድታመንጭም ይፈቅዳል" ብለዋል። ከባህር ጠለል በላይ እስከ 595 ሜትር የግድቡ ከፍታ ድረስ በመጀመሪያ ዙር ውሃ የምታጠራቅምበት ጊዜ ሲሆን ከዚህ በላይ ያሉት የ2ኛ፣ 3ኛ እና ቀጣይ ዙር እስከ 625 ሜትር የውሃ ማጠራቀም ሂደት ምን መሆን እንዳለበትም በስምምነቱ ውስጥ መካተታቸውን ነው ያስረዱት። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ስምምነቱ በውሃ አሞላል ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ በክረምት ወቅት የታችኞቹን አገራት ጉዳት ላይ በማይጥል መልኩ ውሃ ማጠራቀም እንደምትችልና ድርቅ ሲያጋጥም የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ መልኩ አጣጥሞ ውሃ መልቀቅንም ያካትታል። ድርድሩም ሆነ ስምምነቱ በሕዳሴው ግድብ ላይ ብቻ ያተኮረ እንጂ የኢትዮጵያን የወደፊት አጠቃላይ የውሃ አጠቃቀም እንደማያካትት ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም