ቀጥታ፡

ኤምባሲው በኬንያ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 27/2012 በኬንያ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መብታቸው እንዲከበርና ወደ አገራቸውም እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑን በአገሪቷ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለፀ፡፡ ኤምባሲው በተለያዩ ጥፋቶች ተፈርዶባቸው የታሰሩትን ለማስፈታትም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለሰ አለም በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን አስመልክቶ ከኬንያ የማረሚያ ቤቶች አገልግሎት ኮሚሽነር ጀኔራል ዋይክሊፍ ኦጋሎ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ በአገሪቷ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መብት እንዲከበርና የተፈረደባቸውም ምህረት ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከኬንያ ባለድርሻ አካላት በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሷል። ኮሚሽነር ጀኔራል ዋይክሊፍ ኦጋሎ በበኩላቸው ኤምባሲው በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሚያደርገው የቆንስላ ድጋፍ አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ ኤምባሲው ኢትዮጵያዊያኑ እስረኞች ያሉበትን ሁኔታ በመለየት ከሚመለከታቸው የኢፌዴሪ መንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ባለፉት ስድስት ወራት ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገራቸው መመለሱንም ኤምባሲው በመግለጫ ጠቅሷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም