የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ነገ ይካሄዳል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2012 የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት 36ኛው መደበኛ ስብሰባ ነገ በአዲስ አበባ የኀብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ይካሄዳል። ’’ የጦር መሳሪያ ድምጽን ማጥፋት ለአፍሪካ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር’’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል። ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ምክር ቤቱ የቀረበለትን ረቂቅ አጀንዳና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ቅዳሜና እሁድ ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ያቀርባል። በመድረኩ የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለሥልጣናት በተገኙበት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ሪፖርት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በዝግ ውይይት እንደሚደረግ የወጣው መርሃ-ግብር ያመለክታል። እንዲሁም እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር ከጥር እስከ ታህሳስ 2019 ድረስ የህብረቱንና በስሩ ያሉ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ዓመታዊ ሪፖርት እና 14ኛው የአፍሪካ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ድንጋጌ አፈፃፀምን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አመራሮችና ባለስልጣናት በተገኙበት ነገ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋድ ላይ በይፋ ይከፈታል። በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ከስራ አስፈጻሚው ምክር ቤት ሊቀ-መንበር የመክፈቻ ንግግር በተጨማሪ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳፋኪ ማህማት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እንደሚያደርጉ የስብሰባው መርሃ-ግብር ያመለክታል። በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የ55 አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ሲሆን ምክር ቤቱ የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ረቂቅ አጀንዳ፣ የውሳኔ ሃሳቦች እና መግለጫዎችን የሚያቀርብ ይሆናል። በተለይም የ2019 መሪ ሃሳብ በነበረው “አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች” ከግምት ውስጥ ያስገባል፤ ወቅታዊ ዘገባዎችም ይቀርባሉ። እንዲሁም የንዑስ ኮሚቴዎች ሪፖርቶች የስደተኞች የጥናትና ምርምር የአፍሪካ ማዕከል ምስረታ ደንብ ያለበትን ሁኔታ፣ የህግና የፍትህ ጉዳዮች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ እና አጀንዳ 2063 የተመለከቱ ጉዳዮች ይመለከታል። ከአፍሪካ ህብረት ባገኘነው መረጃ መሰረት የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኃላፊነታቸውን ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማ ፎዛ ያስረክባሉ።