ለመሪዎቹ ጉባዔ የመዲናዋን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል - ፌዴራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
ለመሪዎቹ ጉባዔ የመዲናዋን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል - ፌዴራል ፖሊስ
አዲስ አበባ ጥር 27 /2012 ( ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የመዲናዋን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ነገ በመዲናዋ በሚጀመረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የፀጥታ ማስጠበቅ ዝግጅታቸውን አስመልክተው በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የፌዴራል ፒሊስ ኮሚሽን በ33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የጸጥታ ጥበቃውን አስተማማኝ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ እንደገለጹት በሕብረቱ ጉባዔ ለመሳተፍ የበርካታ አገራት ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተጋባዥ እንግዶች ወደ መዲናዋ ይመጣሉ።
ይህን ተከትሎ ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት እንዳይኖር ኮሚሽኑ ከመዲናዋ ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከመከላከያና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል።
ያም ሆኖ የፀጥታና የደህንነት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የሕብረተሰቡ ሁለንተናዊ ትብብር ስለሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ነዋሪ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
እንግዶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ኅብረተሰቡ በተለይም አሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉና ከፀጥታ አካላት ጎን እንዲሰለፉም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው በመዲናዋ የሚካሔደው የኅብረቱ ጉባኤ በሠላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሉን ሊያሳይ ይገባል ብለዋል።
የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳስበው እንግዶች በአጀብ በሚያልፉበት ወቅት ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችንም አሳውቀዋል።
በዚሁ መሰረት ከቦሌ አየር መንገድ-በሚሊኒየም አዳራሽ-ወሎ ሰፈር፣ ከኦሎምፒያ-መስቀል አደባባይ- ብሔራዊ ቤተመንግስት-ግቢ ገብርኤል መታጠፊያ-ሸራተን አዲስ -አራት ኪሎ።
ከቦሌ አየር መንገድ- በሚሊኒየም አዳራሽ-ወሎ ሰፈር፣ ከኦሎምፒያ-ጋዜቦ በአዲሱ መንገድ- ቂርቆስ ታቦት ማደሪያ -ቡልጋሪያ ማዞሪያ-አፍሪካ ሕብረት።
ከፓርላማ መብራት-በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር-ብሄራዊ ቤተመንግስት- በፍል ውሃ-ብሔራዊ ቲያትር- ሜክሲኮ አደባባይ-አፍሪካ ሕብረት።
ከአራት ኪሎ-በሸራተን ሆቴል- ሐራምቤ ሆቴል-በብሔራዊ ቲያትር መብራት ወይም አንድነት መብራት- ሰንጋ ተራ -ዋቢ ሸበሌ- ሜክሲኮ አደባባይ- ትምባሆ ሞኖፖል- አፍሪካ ሕብረት።
እንዲሁም ከቦሌ አየር መንገድ- በሚሊኒየም አዳራሽ- ወሎ ሰፈር- ከኦሎምፒያ-መስቀል አደባባይ-ብሔራዊ ቤተመንግሰት-ግቢ ገብርኤል መታጠፊያ-አራት ኪሎ እንግዶች በአጀብ በሚያልፉበት ወቅት ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
በመሆኑም ከጦር ኃይሎች ወደ ሜክሲኮ አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች በኮካኮላ ድልድይ-በአብነት- ተክለኃይማኖት ወይም በሞላ ማሩ-ጌጃ ሰፈር-ጎማ ቁጠባ።
የቦሌ መንገድ ተጠቃሚዎች ደግሞ በአትላስ-ዘሪሁን ሕንፃ-ሲግናል፣ በቀለበት መንገድ- ቦሌ ሚካኤል ሃኪም ማሞ ወደ ጎተራ፣ በቀለበት መንገድ-መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ-እንግሊዝ ኤምባሲ።
ከቀለበት መንገድ-መገናኛ-አድዋ ጎዳና-አዋሬ-አራት ኪሎ መንገዶችን በአማራጭነት መጠቀም የሚችሉ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጿል።