ወጣቱ የኢትዮጵያዊያን አኩሪ ታሪክና ባህሎች መጠበቅ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ የኢትዮጵያዊያን አኩሪ ታሪክና ባህሎች መጠበቅ አለበት
ደሴ ኢዜአ ጥር 27/2012 ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያዊያን አኩሪ ታሪክና ባህሎች በመረዳት መጠበቅ እንዳለበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን አመለከቱ። ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ሰባተኛው የአድዋ የእግር ተጓዦች ትላንት ደሴ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በአቀባበሉ ስነ ስርዓት ወቅት የተገኙት ዶክተር አባተ እንዳሉት ኢትዮጵያ የበርካታ አስደናቂ ታሪክና ባህል ሃብት ያላት ሃገር ናት።
ለሌሎች ሀገራት ጭምር አስደማሚ የሆነው የኢትዮጵያ አኩሪ ታሪኮችና ባህሎች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የውጭ መጤ ባህሎች በኢትዮጵያውያን ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩና የመበረዝ አደጋ እያጋጠመ በመሆኑ ወጣቱ የቀደምት ኢትዮጵያዊያን ታሪክ በመረዳት መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡት የአድዋ የእግር ተጓዦች በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ሰላም ፣አንድነትንና ፍቅርን በመስበክ እያደረጉት ያለው ጥረት መበረታታትና መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ወጣቶቹ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ለማጎልበት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መላኩ ሚካኤል ናቸው፡፡
"አባቶቻችን በኃይማኖትና በብሔር ሳይለያዩ ዳር ድንበር ጠብቀው ያስረከቡንን አንዲት የጋራ ሀገር የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን "ብለዋል፡፡
የተጓዦቹ አስተባባሪ ወጣት መሃመድ ካሳ በሰጡት አስተያየት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሰባስበው አንድነትን፣ ሰላምንና ፍቅርን እየሰበኩ በእግራቸው ወደ አድዋ እንደሚጓዙ ገልጿል፡፡
63 ሆነው ከአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ መነሻቸውን እንዳደረጉ የተናገረው ወጣቱ ጉዞ ከጀመሩ 17 ቀናት እንደሆናቸውም አመልክቷል።
በተለያዩ ከተሞች ህብረተሰቡ የሚያደርግልን ድጋፍ፣ አቀባበልና አሸኛኘት ብርታት እንደሆናቸውም ጠቁሟል።
ወይዘሮ ትዕግስት ስጦታው በበኩላቸው አንድነትን፣ ፍቅርና አብሮነትን ለመስበክ አምስት ልጆቻቸውን ትተው ከቡድኑ ከተጓዦቹ ጋር በእግር ወደ አድዋ እያቀኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ትክክለኛውን ታሪክ ለማወቅና ለትውልድ ለማስተላለፈ ሁሉም ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዉ፤" ህብረተሰቡ በሚያደርግልን አቀባበልና ድጋፍ የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት መረዳት ችለናል" ብለዋል፡፡
ለአድዋ ተጓዦች የወሎ ዩኒቨርስቲና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ትላንት ደማቅ አቀባበል በማድረግ ዛሬ ሸኝቷቸዋል።