በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በድጋሚ የናዳ አደጋ ተከሰተ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በድጋሚ የናዳ አደጋ ተከሰተ
አርባምንጭ ኢዜአ ጥር 27 /2012 ዓም በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተዉ የናዳ አደጋ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመሩን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅህፈት ቤት ገለፀ ። የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለፁት በጋጮ ባባ ወረዳ ጋፀ ቀበሌ ትናንት ምሽት ድጋሚ የናዳ አደጋ ተከስቷል፡፡ በዚሁም የ31 አባወሯ አባላት የሆኑ 124 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ይህም የተፈናቃዮችን ቁጥር ወደ 170 ከፍ አድርጎታል፡፡ የዞኑ አስተዳደር ለተፈናቃዮች እህል ፤ ዘይትና አልሚ ምግብ ሌሎች የእለት ደራሽ እርዳታ ያደረገ ሲሆን የዞኑ ቀይ መስቀል በበኩሉ 60 ሺህ ብር የሚገመት የአልባሳት ፣ የመጠለያ ሸራ ፣ የመመገቢያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አበርክቷል ። አካባቢው ተራራማ በመሆኑና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ያለማቋረጥ እየጣለ ስለሚገኝ ተጨማሪ 340 የቤተሰብ አባላት የሚያስተዳድሩ 62 አባወሯዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ መሰጠቱን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል ። የዞኑ አስተዳደር የተለያዩ ወረዳዎችን በማስተባበር የሚያደርገው ሰብአዊ ድጋፍ የሚቀጥል ሲሆን ዘላቂ መፍትሄ ለማመቻቸት ከደቡብ ክልልና ከፈደራል አደጋ ስጋት ተቋማት ጋር እየተነጋገረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በአካባቢው ባለፈው ሐሙስ በተከሰተው ናዳ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉና 46 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል።