ቀጥታ፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሲያጓጓዝ የነበረ አሽከርካሪ ተያዘ

ጥር 26/2012 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታችአርማጭሆ ወረዳ በህገወጥ መንገድ አስር ክላሽንኮቭ ጠብመንጃና ከ5ሺ በላይ የሽጉጥ ጥይቶችን ሲያጓጉዝ የነበረ አሽከርካሪ መያዙን የወረዳው አስተዳደር ጸጥታ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አንተነህ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት ጠብመንጃዎቹና ጥይቶቹ የተገኙት በተሽከርካሪ ላይ እንደተጫኑ ዛሬ ጠዋት በሳንጃ ከተማ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ኬላ በተደረገ ፍተሻ ነው፡፡ በጉምሩክ ሰራተኞች፣ በፖሊስና በልዩ ኃይል አባላት የጋራ ቅንጅት በተደረገው ፍተሻ የተገኘው  ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው ወደ ጎንደር በድብቅ ሊገባ የነበረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ጭኖ ሲያጓጉዝ የነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -15582 አማ  "ፒ ካፕ "ተሸከርካሪ መሆኑን ጠቅሰው፤  አሽከርካሪው ተይዞ ጉዳዩ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አመልክተዋል። ጠብ መንጃዎቹና ጥይቶቹ መነሻቸው ጠገዴ ወረዳ ሰሮቃ ከተማ እንደሆነ ጠቁመው በኬላው የሚያዙ አብዛኞቹ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ከሱዳን እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም