ቀጥታ፡

ስለታገቱት ተማሪዎች የተሟላ መረጃ አለመኖሩ ችግሩ በፍጥነት እንዳይፈታ አድርጓል ... የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2012 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስለታገቱት ተማሪዎች የተሟላ መረጃ አለመኖር ችግሩ በፍጥነት እንዳይፈታ ማድረጉን ገለጸ።

በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ 14 ተማሪዎችና ሌሎች አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች እገታ ዙሪያ ኢዜአ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ በእገታው ዙሪያ የተሟላ መረጃ አለመኖሩ ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ጉዳዩን ከሰማበት ጊዜ አንስቶ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ችግሩ ያጋጠመበት አካባቢ የታጠቀ ቡድን የሚንቀሳቀስበት መሆኑ የችግሩን መፍትሄ እንዳወሳሰበው ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም ''እንደዚህ አይነት የአጋች ታጋች ድራማ በሚከሰትበት ወቅት ዋነኛው ትኩረት መሆን ያለበት የታገቱ ሰዎች ህይወትና ደህንነት ላይ አደጋ ሳይደርስ የታገቱትን ሰዎች ነጻ ማውጣት መሆን መቻል አለበት'' ብለዋል።

በመንግስት በኩል መረጃ ሳይሰጥ ጉዳዩ በሚስጥራዊነት ተይዞ መቆየቱ ከህብረተሰቡ ለመደበቅ ታስቦ ሳይሆን ከጉዳዩ ባህሪ አንጻር በመነሳት እንደሆነም ገልጸዋል።

ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝም በእገታው ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑንና ኮሚሽኑም በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ባሉት አማራጮች ሁሉ ተጠቅሞ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነና በቅርቡም መፍትሄ እንደሚያገኝ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለኢዜአ ሙያዊ አስተያየታቸውን የሰጡ የህግ ባለሙያዎች ''እንዲህ ያለው ድርጊት ሲፈጸም ከምንም በላይ በመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑት የችግሩ ሰለባ የሆኑት ወላጆችና ቤሰቦች ናቸው'' ብለዋል።

በመሆኑም፣ መንግስት በቀዳሚነት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቁ ተቀዳሚ ተግባሩ ሲሆን ህግን ጥሰው እንዲህ ያለ ድርጊት የሚፈጽሙት ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል።

ጉዳዩን ለቀናት ማፈን፣ ግልጽ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ አለመስጠትና እርስ በርሱ የሚጋጭ መረጃ ማሰራጨት በተጎጂ ቤተሰቦች ላይ ይበልጥ  ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በወቅቱ የተጣራ መረጃ መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

''ከታጋቾቹ መካከል ቁጥራቸው ላቅ ያለ ሴቶች በችግሩ ውስጥ ስለሚገኙ፣ ዛሬ ነገ ሳይባል ጉዳዩን የሚከታተለው ኮሚቴ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት ማድረግ አለበት' ብለዋል።  የ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም