የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለተቋረጡና ለተጓተቱ የህንጻ ፕሮጀክቶች መጀመር ምክንያት ሆኛለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለተቋረጡና ለተጓተቱ የህንጻ ፕሮጀክቶች መጀመር ምክንያት ሆኛለሁ አለ
አዲስ አበባ ጥር (ኢዜአ) 26/2012 ''ለሰባትና ከዚያ በላይ ዓመታት ለተቋረጡና ለተጓተቱ የህንጻ ፕሮጀክቶች መጀመር ምክንያት ሆኛለሁ'' ሲል የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወር አፈጻጸም አስመልከቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥቷል፡፡ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ የኮንስትራክሽና ግንባታዎች አገራዊ ፍላጎትን ማሟላት እንዲችል በተገቢው ወጪ፣ ጊዜና ጥራት መፈጸማቸውን ይቆጣጠራል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ጋማሽ በ15 የህንጻ ግንባታዎችና 11 የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የቁጥጥር ስራዎችን ባለስልጣኑ ማከናወኑን ገልጸው፤ ''በተደረገው ቁጥጥር ለሰባት ዓመታትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ግንባታቸው የተጓተቱና የቆሙ አራት የህንጻ ፕሮጀክቶች ስራቸው እንዲጀመር ባለስልጣኑ ምክንያት ሆኗል'' ብለዋል፡፡ በቂ ዋስትና ሳይቀርብባቸው የቅድመ ክፍያ የተፈጸመባቸውና ያለአግባብ የተፈጸሙ ክፍያዎችን እንዲመለሱ በማድረግ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነን የመንግስት ገንዘብ ማዳን ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በግማሽ ዓመቱም ቁጥጥር ከተደረገባቸው 450 የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ውስጥ 19 የሚሆኑት ህጋዊነትን ያላሟሉ በመሆናቸው የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉን አቶ ማተቤ አመልክተዋል፡፡ በተደረገው የግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ቁጥጥርም ያለአግባብ ሊወጣ የነበረን ከ800 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ማዳን መቻሉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በባለስልጣኑ የግንባታ ስራዎች ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እንዳለው ተመስገን በበኩላቸው የኮንስተራክሽን ኢንዱስትሪው እጅግ ጥልቅ፣ ውስብስብና አድማስ ተሻጋሪ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከእያንዳንዱ አገራዊ ልማት በስተጀርባ ይህ የኮንስትራክሽና ኢንዱስትሪ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የግንባታው ኢንዱስትሪም ከግብ ሊደርስ የሚችለው የሰራተኞች ደህንነት በበቂ ሁኔታ ሲረጋገጥ በመሆኑ ባለስልጣኑም በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 በአንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 18 መሠረት ባለፈው ዓመት የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡