ቀጥታ፡

በአሶሳ ከተማ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር እየተረጋጋ መሆኑ ተገለጸ

አሶሳ ሰኔ 19/2010 በአሶሳ ከተማ  ትናንት ምሽት ተቀስቅሶ የነበረው የፀጥታ ችግር በአሁኑ ወቅት እየተረጋጋ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲንሳ በየነ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ዛሬ በአሶሳ ከተማ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገሪቱ እያመጡት ላለው ለውጥ የምስጋና የድጋፍ ሰልፍ ለማካሄድ ታስቦ ነበር፡፡ በከተማዋ ሊካሄድ የታሰበውን ሰልፍ ለማደናቀፍም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች  ትናንት ማምሻውን በፈጠሩት ሁከት አስራ አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡ በከተማዋ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በጉዳዩ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ አርባ ስድስት ግለሰቦችም ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የህግ አስከባሪዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ባደረጉት ጥረት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር እየተረጋጋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም