የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

60
አዲስ አበባ  ጥር (ኢዜአ) 26/2012 የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል በቻይና የተባበሩት ማዕድን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሊቀመንበር ሚስተር ሺጂንግ ዛንግ የተመራ ልዑክን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው ባደረጉት ንግግር ''ቻይና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ጉልህ ድርሻ ካላቸው አገሮች አንዷ ናት'' ብለዋል። ቡድኑ በኢትዮጵያ የተለያዩ አገልግሎቶችን የያዘ ዘመናዊ መንደር ለመገንባት ፍላጎት ማሳደሩ በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለውና መንግስትም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡ ሚስተር ሺጂንግ ዛንግ በበኩላቸው ድርጅታቸው በቻይና የተለያዩ ሁሉን አቀፍ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታ ላይ የተሰማራ ድርጅት እንደሆነና በፓርኩ ውስጥ በርካታ ኤሌክትሮኒክሶችና ሶፍትዌሮችን እንደሚያመርት አብራርተዋል፡፡ ሚስተር ሺጂንግ አክለውም በኢትዮጵያ ሊገነቡት ያሰቡት ፓርክ ሆቴሎችና አፓርትመንቶችን የሚያካትትና በአዲስ አበባ መሃል ከተማ ላይ ቢሆን ፍላጎታቸው እንደሆነም ገልጸው። መንግስት ለዚህ ሰፊ የኢንቨስትመንት እቅድ አስፈላጊውን የመሬትም ሆነ ሌሎች ድጋፎችች እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም