ቀጥታ፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢህአዴግ በተግባር መፍረሱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ጥር 26/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ( ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ህጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት ኢህአዴግ  በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ያሳወቀ ሲሆን በሌላ በኩል ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ የግንባሩን መፍረስ አስመልክቶ የንብረት ክፍፍል እንዲካሄድና ውሳኔ እንዲሰጥበት መጠየቁን ቦርዱ አስታውሷል፡፡ የግንባርን መፍረስና ያለመፍረስ ጉዳይ  የመወሰን ስልጣን ያለው የቦርዱ ብቻ መሆኑን የስታወቀው ውሳኔው የኢህዴግ ግንባርና ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው ህጋዊ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በግንባሩና በህወሓት የቀረቡትን  የጽሁፍ ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ እና የግንባሩ አባል ሶስት ፓርቲዎች  አዲስ ውህድ ፓርቲ መመስረታቸውን ተከትሎ የኢህዴግ ግንባር  በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ደኢህዴን ብልጽግና የሚባል ፓርቲ በመመስረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በህጉ መሰረት በብልጽግና እና በህወሓት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን  የንብረት ክፍፍል ሁኔታ አስመልክቶ  የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡ 1.ብልጽግና እና ህወሓት የኢህአዴግ ንብረትና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ ቡድን በጋራ እንዲሰይሙ፤ 2.በኢህአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፤ 3.ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት 3/4ተኛው ድርሻ ለብልጽግና ፓርቲ አንድ አራተኛው ደግሞ ለህወሓት እንዲሆንና በዚያ መሰረት ክፍፍሉ እንዲጠናቀቅ፤ 4.ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በህጉ መሰረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ  መወሰኑን የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም