ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ቆላማ ስፍራዎች ስንዴ እንዲመረት እስራኤል ሙያዊ ደጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ ጥር 26/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ቆላማ በሆኑ ሥፍራዎች ስንዴ በስፋት ለማምረት የምታደርገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ እስራኤል ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በእስራኤል ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተደረሱት ሌሎች ሥምምነቶች ላይም ተጨባጭ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል። አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ከግምት በማስገባት በበርካታ የትብብር መስኮች ላይ አጋርነቷን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የምታከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ በመስኖ ልማትና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ ዝርያዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ላለፉት 13 ዓመታት ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩስኤይድ) ጋር በመተባበር ሲሰሩበት የቆዩትን ፕሮጀክት ለመንግሥት ሊያስተላልፉ መሆኑን አስረድተዋል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የእቅድ አካል የሆነውን በዝቅተኛ ስፍራዎች ስንዴ የማምረት ውጥን ለመደገፍ አዲስ የግብርና የትብብር መስክ ይፋ ሊያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፈው ሣምንት የዘርፉ ባለሙያዎች ከእስራኤል መጥተው ዘር መዝራትና የመስኖ ሥራ የሚካሄድባቸውንና የልህቀት ማዕከል ስፍራዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን የአሳ ዘርፍ ልማት አቅም ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም በዚህም ላይ የትብብር አድማሱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሞራቭ ጠቁመዋል። ከዛ በዘለለ ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር የደረሱበትን ሥምምነት አፈጻጸም በተመለከተም ተጨባጭ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለአብነትም ከላይ የተጠቀሰው የግብርና ዘርፍ አዲስ የትብብር ምዕራፍ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው በሳይንስና ኢኖቬሽን ዘርፍም የእስራኤል ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተናግረዋል። እነዚህ የእስራኤል ባለሙያዎች በቆይታቸው በኢትዮጵያ የሳይንስና ኢኖቬሽን ምቹ ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችል ከባቢ በማጥናት ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማቅረባቸውን ጠቁመዋል። ይህንንም በቅርቡ እየተከታተሉ መሆኑንና በሳይበር ቴክኖሎጂም የኢትዮጵያ የዘርፉ ባለሙያዎች ወደ እስራኤል በመሄድ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። በሁለቱ መሪዎች በተደረሰው የፍላጎት ሥምምነት መሰረት በስፔስ ሳይንስ ላይ ትብብሩን ለማጠናከር ከሚመለከተው ተቋም ጋር  ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የምታደርገው ምርጫ ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት እስራኤል ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆምና ለመርዳትም ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። እስራኤል በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋጥ በተለይም ሽብርተኝነትን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሩ ገልጸዋል። በጥቅሉም የአገራቱ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና የትብብር አድማሱም እየሰፋ መምጣቱን ጠቁመው ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደሩ አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያና እስራኤል የሺህ ዓመታት የሕዝብ ለሕዝብ ጠንካራ ግንኘነት ያላቸው ሲሆኑ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1955 ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም