የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በኳታር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በኳታር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) ከኳታር ኮን ግሩፕ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ኳታር በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ። በዶሃ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ፎረም ላይ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያን ጨምሮ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሀላፊ አምባሳደር አብዱራህማን አልዶሶሪ ተገኝተዋል። በዚህ ወቅት በሁለቱ አገራት ስላለው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርና ስለምቹ ሁኔታዎች ገለጻ መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የንግድ መዳረሻ ከሆኑት የአፍሪካ አገሮች መካከል በመጀመሪያዎቹ ተርታ የምትገኝ መሆኗን አስታውሰዋል። የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የሚሰጡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችንና ድጋፎችን በተመለከተም አገሪቱ ለኢንቨስተሮች ምቹ ያደረጓትን ዋና ዋና ምክንያቶች በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር አብዱራህማን አልዶሶሪን በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ተነሳሽነት አድንቀው የኳታር ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል። በፎረሙ ላይ 120 የሚጠጉ የኳታር ኢንቨስተሮች፣ የተለያዩ ኩባንያ ባለቤቶችና ሃላፊዎች፣ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።