በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጎርፍ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቀለ

256
ጥር 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ማለዳ ላይ በተከሰተ ጎርፍ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ  ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሰግድ ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት ጎርፉ  የተከሰተው በወረዳው  ኤልጎ፣  ቆላ ሼሌ እና ሼሌ ሜላ ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡ ትናንት ምሽት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የስሌ እና ሴጎ ወንዞች ሞልተው ከመደበኛ መስመራቸው በመውጣት በቀበሌዎቹ የመኖሪያ መንደርን አጥለቅልቀዋል። በዚህም ምክንያት 13 ሺህ 885 ሰዎች መኖሪያ ቤታቸው በውሃ በመዋጡ መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በ32 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ቋሚ ሰብል ማውደሙን አመልክተዋል። ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለማመቻቸት የዞኑ  አስተዳደር ጥረት እያደረገ መሆኑንም  ጠቁመዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም