ቀጥታ፡

በሶኮሩ ወረዳ በሚገኝ የሀይል ማስተላለፊያ (ትራንስፎርመር) ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ በሚገኝ የሀይል ማስተላለፊያ (ትራንስፎርመር) ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ። በአሁኑ ሰአት የሀይል ማስተላለፊያው ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢዜአ ገልጸዋል። እሳቱ እንዲጠፋ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሙያዎች፣ ከጅማ የእሳት አደጋና መቆጣጠሪያ ማዕከል ባለሙያዎች፣ ከጅማ አየር መንገድና ሲቪል አቪዬሽን፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የሶኮሩ ወረዳ የአስተዳደር አካላትና የአካባቢው ነዋሪ ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ እንዳደረጉ ተናግረዋል። በተደረገው ርብርብ እሳቱ ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት በቁጥጥር ስር እንደዋለና የአካባቢው ማህበረሰብና የተለያዩ አካላት እሳቱን ለመቆጣጠር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በሶኮሩ የሃይል ማስተላፊያ በተቃጠለው ትራንስፎርመር ምትክ ሌላ ትራንስፎርመር እንደሚገኝና ትራንስፎርመሩ እስኪተከል ድረስ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት የተቋረጠባቸው ከተሞች የኤሌትሪክ ሃይል እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል። ዛሬ ማለዳ 1 ሰአት ከ 45 ደቂቃ በግልገል ጊቤ አንድና ሁለት መካከል በሚገኝ ባለ 400 እና 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ ባለ 250 'ሚዲየም ቮልቴጅ አምፒር' ትራንስፎርመር ላይ የእሳት አደጋ መድረሱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም