ቀጥታ፡

ባለኃብቶች በኢነርጂ ልማት ስራዎች እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ጥር 26/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከናወኑ የኢነርጂ ልማት ስራዎች ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። በ451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቋል። በምረቃ ስነ-ስረአቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ''በዓመቱ መጀመሪያ የጀመርነውን ጨርሰን ሪቫን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም ብለን ነበር'' ሲሉ ከዚህ ቀደም ያስተላለፉትን መልዕክት አስታውሰዋል። የገናሌ ዳዋ 3 ፕሮጀት ተጠናቆ ለስራ ዝግጁ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የ'እንኳን ደስ አላችሁ' መልእክት አስተላልፈዋል። ''የገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከሚያበረክተው የኢነርጂ አስተዋጽኦ ባሻገር የጉጂና የባሌ ህዝቦችን ትስስርና አንድነት የሚያሳይ ነው'' ብለዋል። የኢትዮጵያ የወደፊት ልማት በውሃ ላይ ያተኮረ እንደሆነና ውሃን በቀላሉ የምንገለገልበት እንደሆነው ሁሉ የውሃ ሃብትን አገሪቱ ካጣች የምንጣላበት ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ በበርካታ ቦታዎች የውሃ ሃብት በስፋት ያለ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ተናግረዋል። እንደ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ እጅጉን ከሚያስፈልጓት ነገሮች አንዱ ኢነርጂ በመሆኑ በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር መንግስት በቅርበት ይሰራል። በመሆኑም የገናሌ ዳዋ 3 መመረቁ ለገናሌ ዳዋ 6 ግንባታ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን ገልጸው ባለኃብቶች ለገናሌ ዳዋ 6 ግንባታና ለኢነርጂ ልማት ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል። ይህንን ፕሮጀክት ለማከናወን ከውጪ ባለኃብቶች ብዙ ጥያቄ ቢቀርብም ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል። ''አዋጭነቱን ከግምት በማስገባትና በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ለምትፈልጉ ባለሃብቶች የገናሌ ዳዋ 6 ልማት ላይ በመሳተፍ የልማቱ ተሳታፊ በመሆን በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኢነርጂ ችግር ለመፍታት አስተዋጽኦ ማበርከት አለባችሁ'' ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። ፍላጎቱ ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ፈጥነው ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር ትስስር ፈጥረው ወደ ስራ መግባት የሚችሉበት ዝግጅት እንዳለም ጠቁመዋል። የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል ሃብት ላይ በስፋት በመስራት ኢነርጂን ተደራሽ እንደሚደረግ ገልጸዋል። በቂ ኢነርጂ ካልተዳረሰባቸው አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ በባህላዊ ዘዴ የኢነርጂ ፍላጎቱን ለማሟላት ጥረት የሚያደርገው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን አውስተዋል። ''ከብሔራዊ ኃይል ወይም ቋት ጋር የተገናኘውን 35 በመቶ እንዲሁም ከጎረቤት በመቀጠል ኤሌክትሪክ የሚያገኘው ህዝብ 45 ከመቶ ብቻ ነው'' ብለዋል። ሆኖም በቅርቡ ከተጀመሩት ፕሮግራሞች አኳያ ኤሌክትሪክ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ ከሚደረገው ጥረት መካከል የኢነርጂ ተደራሽነት በፍጥነት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ''ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ተያይዞ የሃይል አቅርቦትና ፍላጎትም እንዲሁ እድገት አሳይቷል'' ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዓመት 19 ከመቶ በላይ ቢሆንም በበርካታ ችግርና ማነቆ የተሳሰረ በመሆኑ የሚቀርበው የኤሌክትሪክ መጠን ከስምንት በመቶ ሊበልጥ እንዳልቻለ ጠቅሰዋል። ለዚህም የፋይናንስ እጥረት፣ የኢነርጂ መሰረተ ልማት መጓተትና የአጠቃቀም ችግር ተጠቃሽ መሆኑን አክለው፤ ''ከታዳሽ ኃይሎች የሚገኝ ኢነርጂን ለመጠቀም በትኩረት ይሰራል'' ብለዋል። ሚኒስትሩ በግንባታው የተሳተፉ የአገር ውስጥና የውጭ ሙያተኞች ላበረከቱት ሙያዊ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። በዛሬው እለት የተመረቀው የገናሌ ዳዋ 3 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሶስት ተርባይኖች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው። ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ 254 ሜጋ ዋት ወይም 1640 ጌጋ ዋት ሰዓት ኃይል በዓመት የሚያመነጭ ይሆናልም ተብሏል። የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል  ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት የሚገባው ይርጋለም ከሚገኘውና ባለ 400 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ አማካኝነት እንዲገናኝ ተደርጓል። በአጠቃላይ ግድቡ 110 ሜትር ቁመት፣ 426 ሜትር ርዝመትና 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ውሃውን የሚያስተላልፍና ከግድቡ ጋር የተገናኘ 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የውሃ ማስገቢያ ዋሻ ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን በጣቢያው ላይ 380 ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ መልቀቂያ ዋሻ ተገንብቷል። ለግንባታው 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድርና 40 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው። ግንባታው የተጀመረው እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ2003 ሲሆን ለ1 ሺህ 500 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠረ እንደነበርም ተገልጿል። የገናሌ ዳዋ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጉጂና ባሌ ዞኖች በሚገኙ የመዳ ወላቡና ጎሮዶላ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢ የሚገኝ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም