የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ

118
አዲስ አበባ፣ ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ)  የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከፈተ። ‹‹የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ግንባታ›› በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር ለተከታታይ 7 ቀናት ይቆያል። የዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተሞክሮእንዲለዋወጡ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲመለከቱ፣ የውጭ ተኪ ምርት አምራቾችንና ፈላጊውን ማገናኘት የኤግዚቢሽኑና ባዛሩ ዓላማ እንደሆነ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አቶ አስፋው አበበ ገልጸዋል። ተኪ ምርቶችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በማስተዋወቅ ለአምራቹ የገበያ እድል መፍጠርና ህብረተሰቡ አገር በቀል ምርት የመጠቀም ባህሉን ለማጎልበት የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታአቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ በበኩላችው ኢግዚቢሽኑ "የአገራችን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የደረሠበትን ደረጃና ወቅታዊ አቅም በቅርበት ለመመልከት" አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል። ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበርና የተጓተተ የአገልግሎት አሰጣጥመታየቱን አስታውሰው ይህንንም በመፍታት ዘርፉን ለማገዝ አምራቾች ማምረቻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበት አሰራር እንዳለ ጠቁመዋል። በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የአገር ውስጥ ምርት የሆኑ የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓትና የኬሚካል ውጤቶችና የጌጣጌጥ ምርቶች ለእይታና ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከኢንዱስትሪ ዘርፉና ከአነስተኛና መካከለኛ ዘርፍ 143 ፣ የልማትና አጋር ተቋማት እንዲሁም አራት ዩኒቨርሲቲዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በባዛሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስርን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም