ቀጥታ፡

የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ የሽብር ቡድኖች የሞከሩትን ጥቃት የመከላከያ ሠራዊት አክሽፎታል

አዲስ አበባ፣ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሽብር ቡድኖች በር መክፈቱን ተከትሎ የተቃጡ ጥቃቶችን የመከላከያ ሠራዊት ማክሽፉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን የተናገሩት ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለተለያዩ የሽብር ቡድኖች በር ቢከፍትም የመከላከያ ሠራዊት የተቃጡ የሸብር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል። በአገሪቷ ክልሎች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ አባላትን በመመልመልና ኔትወርክ በማስፋት ጥቃት ለመሰንዘርና አጋጣሚውን በመጠቀም የአገሪቷን ህልውና ለማዳከም ሰፊ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። "ከምንጊዜውም በላቀ ኢትዮጵያን የማንኮታኮትና የማዳከም ጊዜ አሁን ነው በማለት የተጀመረውን ለውጥ  ለማደናቀፍ ከውጭና ከአገር ውስጥ ሴራውን በገንዘብና በቴክኒክ በመደገፍ የአገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ከፍተኛ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል'' ነው ያሉት። እነዚህን ጉዳዮች ለመመከት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የደህንነት ተቋማት ከፍተኛ ስራ መስራታቸውንም ተናግረዋል። እነዚህንና መሰል ችግሮችን በወቅቱ መፍታት ባይቻል ኖሮ በአገሪቷ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ያጋጥም እንደነበርም ነው የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የአገሪቷን ህልውና ለማስከበር ቀዳሚው ተግባር የውስጥ ሠላምና ልማትን በማረጋገጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት ነው። ለዚህም መንግስት ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።                                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም