እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ በ28ኛና 29ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብሮች ላይ ማስተካካያ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ በ28ኛና 29ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብሮች ላይ ማስተካካያ አደረገ
አዲስ አበባ ሰኔ19/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁለተኛ ጊዜ በ28ኛና 29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብሮች ላይ የቀን ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ መጀመሪያ ባወጣው መርሃ ግብር የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲሁም የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳሉ ተብሎ ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች የመርሃ ግብር ለውጥ ማድረግ በማስፈለጉ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2010 ዓ.ም የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የሊግ ኮሚቴው መግለጹ ይታወሳል። ፌዴሬሽኑ በተስተካካይ ጨዋታዎች ምክንያት በ28ኛና 29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብሮች ላይ በድጋሚ ማስተካከያ ማድረጉን አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከወልዲያ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰዓት ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በዚያው ዕለት ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይካሄዳል። ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌትሪክ ከፋሲል ከተማ ከቀኑ 9 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ 11 ሰአት ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በቅደም ተከተል ሰኔ 24 ቀን 2010 ከቀኑ 9 ሰአትና ከቀኑ 11 ከ 30 ላይ የሚካሄድ ይሆናል። ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይከናወናል። በክልል ከተሞች ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከደደቢት፣ በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከመቀሌ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ እንዲጫወቱ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር። አሁን በተደረገው ማስተካከያ በክልል ከተሞች የሚደረጉት ጨዋታዎች ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በተመሳሳይ ዘጠኝ ሰአት የሚደረጉ ይሆናል። በ29ኛ ሳምንት ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በመቐለ ስታዲየም መቐለ ከተማ ከኢትዮ-ኤሌትሪክ፣ ፋሲል ከተማ በሜዳው ከኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ከአርባንጭ ከተማ፣ ሃዋሳ ላይ ሃዋሳ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ከተማ በሜዳው ከቅዱስ ጊዮርጊስና በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከጅማ አባጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሊጫወቱ መርሃ ግብር ወጥቷል። አሁን በተደረገው ማስተካከያ የ29ኛ ሳምንት የክልል ጨዋታዎች ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በተመሳሳይ 9 ሰአት ላይ ይደረጋሉ። በ29ኛው ሳምንት ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ከወልዲያ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ጨዋታቸውን በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከመከላከያ ከቀኑ 9 ሰአት የሚያደረጉት ጨዋታዎች ባሉበት መጀመሪያ በተስተካከለው መርሃ ግብር መሰረት ይካሄዳል።