ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት የመንግስት በጀት አልወጣበትም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት የመንግስት በጀት አልወጣበትም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ከመንግስት ወጪ ሳይወጣ ከባለሀብቶችና ከውጭ አገራት በተገኘ ድጋፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሰጡት ማብራሪያም አዲስ አበባን በማስዋብ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በመገንባት ላይ የሚገኘው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ከባለሀብቶችና ከውጪ አገራት በተገኘ ድጋፍ የሚሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
''ፕሮጀክቱ አገርንና አካባቢን የማስዋብ ስራ እንጂ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተብሎ የሚሰራ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው ይገባል'' ብለዋል።
በዚህ በጎ ተግባር ባለሀብቶች አምስት ሚሊዮን ብር በማውጣት ለገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀ የእራት ማዕድ መታደማቸውን እና የውጭ አገራትም ድጋፍ በማድረግ ለፕሮጀክቱ ጥሩ ደረጃ መድረስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር በከተማዋ የሚስተዋለውን የመዝናኛና የመናፈሻ ችግር እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ እያፈረሱ ያሉ አካላትን ማህበረሰቡ እንዲከላከልና እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል።