ቀጥታ፡

ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትለው እስከሰሩ ድረስ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ድምጽ እንደሚሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ-ምግባርንና ህግን አክብረው እስከሰሩ ድረስ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ድምጽ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጹ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "ጋዜጠኞች ሙያቸውን የሚያከብሩና የሚሰሩትን ስራ ከፖለቲካ ጋር የማይቀላቅሉ መሆን አለባቸው'' ብለዋል።

''ነገር ግን ጠዋት ጠዋት ጋዜጠኛ ከሰዓት ደግሞ ፖለቲከኛ ከሆኑ ችግር ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ-ምግባርንና ህግን ተከትለው ከሰሩ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ድምጽ ይሆናሉ'' ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ ጋዜጠኞች ያሻቸውን የመናገር አውድ ያገኙበት ጊዜ እንደሆነ አንስተው፤ መንግስትን በመቃወም የተነሳ መታሰር ቢኖር ኖሮ ተጨማሪ እስር ቤቶች ያስፈልጉ እንደነበር ተናግረዋል።

ብዙ አማራጭ ድምጽ መስማት ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው፤ መንግስትም ቢሆን የሚመከርበት፣ የሚገሰጽበትና የሚተችበት ከዚያም ብዙ ትምህርት የሚወስድበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ሁሉ ነገር ፖለቲካና ድራማ  ከሆነ ጉዳት ስለሚያመጣ ይህን አስታርቆ መስራት ከሙያተኛው የሚጠበቅ መሆኑን አሳስበዋል።

የማህበራዊ ሚዲያውን እንቅስቃሴና የመረጃ ስርጭት ሳይጨምር ለውጡ ከመጣ ወዲህ ከዚህ በፊት ተዘግተው የነበሩ ሚዲያዎች መከፈታቸውንና ኢትዮጵያ ውስጥ 50 የሚጠጉ የሬዲዮና 31 የሚሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢዎች አሁን ላይ መኖራቸውን አስታውሰዋል ።

አሁን አሁን በጣም በርካታ የሚዲያ ተቋማት በአገሪቷ እየሰፉ መሆኑንና ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ ለማድረስ በሚዲያዎቹ በኩል ህግን ተከትሎ መስራት ላይ በመንግስት በኩልም መረጃ ሰጥቶ እነሱን መደገፍ ላይ ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በዘርፉ የሚስተዋለው ለውጥ እንዳለ ሆኖ መረጃን በመቀበልም ይሁን በማሰራጨት በኩል ሰፊ ችግር በመኖሩ ተጨማሪ ስራ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም