ቀጥታ፡

መንግስት በውጭ አገራት የተደበቁ የአገር ሃብቶችን ለማስመለስ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

አዲስ አበባ፣ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) መንግስት በውጭ አገራት የተደበቁ የአገር ሃብቶችን ለማስመለስ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 29 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ወደ መንግስት ካዝና መግባቱንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከምክር ቤት አባል ከኢትዮጵያ ተመዝብሮ በውጭ አገሮች ያለውን የአገር ሃብት ለማስመለስ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረትና በአገር ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ሃብት ወደ መንግስት ካዝና ስለመግባቱ ማብራሪያ ተጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም መንግስት በውጭ ያለውን ሃብት ለማስመለስ ከውጭ አገራት መንግስታት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ''አለም ዓቀፍ ተቋማትና ባንኮች የአገርን ሃብት ለማስመለስ ትብብር እንዲያድርጉ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥረት እየተደረገ ነው'' ብለዋል። ''አንዳንድ አገሮች ሃብቱ እንዳለ ካረጋገጡና ሃብቱን ለማስመለስ እገዛ እንደሚያደርጉ ከተናገሩ በኋላ ይሄ አካሄድ የአገራችንን ባንኮች ስራ ይጎዳል በማለት ወደ ኋላ ተመልሰዋል'' ብለዋል። ነገር ግን ሃብቱን ከምንመልስ ኢትዮጵያን በተለየ ሁኔታ እናግዝ በማለት ሃሳባቸውን ያቀረቡ እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሃብቱን ለማስመለስ እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ አገራት የመኖራቸውን ያህል አንዳንድ አገራት መረጃውን ለመስጠት ፈቃደኝነት እንደጎደላቸው ጠቁመዋል። በውጭ አገር የመንግስት ገንዘብ እንዳለ የተረጋገጠ ሲሆን ይህንን ለማስመለስ ግን ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ህገ-ወጥ ገንዘብ፣ ማዕድንና አልፎ አልፎ የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን ለመከላከል በርካታ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል። እስካሁንም 14 ኪሎ ግራም ወርቅና 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተይዞ ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባቱን ገልፀዋል። ''ተይዞ ወደ መንግስት ካዝና ያልገባ ሃብት እንዳለ መረጃ የለኝም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መረጃው ያላቸው የምክር ቤቱ አበላትና ሕዝቡ ለመንግስት ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም