ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ የምታደርገው ድርድር ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ የምታደርገው ድርድር ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ጥር 25/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሕድሴ ግድብን በተመለከተ የምታካሂደው ድርድር ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የሕዳሴ ግድብ ድርድር የደረሰበት ምዕራፍ አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደገለጹት የግድቡ ድርድር ሳይጠናቀቅ ጥቅም ተከብሯል ወይም አልተከበረም ማለት አይቻልም። የታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቡን በሚመለከት ሕጋዊ ጥያቄ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ላለፉት ስምንት ዓመታት አድካሚ ውይይት ሲደረግ ቆይቶ እንዳልተቋጨ ጠቁመዋል። የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሦስቱ አገራት እየተደራደሩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቱ ብቻቸውን በሚያደርጉት ውይይት መልስ ያልተገኘባቸው ጥያቄዎች መልስ እያገኙ መሆኑን አስታውቀዋል። ''የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ድርድሩን ጨርሶ ስምምነት ለመፈራረም ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር'' ያሉት ዶክተር አብይ ፊርማው እንዲዘገይ የሰጡትን ትዕዛዝ ተከትሎ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንትና ትሬዥሪ ሚኒስትር እንዲሁም ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ መወያየታቸውን ገልጸዋል። በውይይቱም የኢትዮጵያ መንግስት በዲፕሎማሲ መርህና ሕግ እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምን መሆኑን ማብራራታቸውን ጠቁመዋል። ግብፅ ኢትዮጵያ ስትጠቀም ጉዳት እንዳይደርስ የመጠየቅ መብት እንዳላት ሁሉ ኢትዮጵያም ውኃን የመጠቀም መብት እንዳላት ከግምት ሊገባ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል። በድርድሩ የአሜሪካና የዓለም ባንክ አቋም ግብጽና ኢትዮጵያ ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው ነገር የሚበዛ ስለሆነ ጉዳዩ በስምምነት ተቋጭቶ ውኃን በጋራ መጠቀም፣ ልማትን በጋራ ማልማት፣ ድህነትን በጋራ የመቀነስ ሂደቱ እንዲሳለጥ ይህን ካደረጉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ብለዋል። ድርድሩ በአሁኑ ወቅት የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የደረሰ ሲሆን በሁለቱም ወገን ያሉ የሕግ ባለሙያዎች ሰፊ ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል። በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ባለሙያዎች፣ የውሃ ቴክኒክ ሰዎችና ሚኒስትሮች አገራቸውን ወክለው ላደረጉት ከፍተኛ ኃላፊነት የተሞላበት አስተዋጽኦም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል። ''ኢትዮጵያን በመሰረቱ በሚጎዳ ነገር ላይ የሚወስን መንግስት ኢትዮጵያ ኖሯት አያውቅም ወደ ፊትም አልጠብቅም፤ ኢትዮጵያን ለመጥቀም ጎረቤቶቿን የሚጎዳ ስራ ኢትዮጵያ አትሰራም'' ነው ያሉት። አገሪቷ ሶማሊያ ውስጥ ገብታ የምትሞተው ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትም ጥቅም መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አብይ 'ዓለም አቀፍ ሕጉን ተከትሎ ድርድሩ በአጭር ጊዜ ይቋጫል የሚል እምነት አለኝ' ብለዋል። የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር እንደማይደረግም አረጋግጠዋል።