ባለፉት ስድስት ወራት ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ ጥር 25/2012 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ ዶክተር አብይ ማብራሪያ የተፈጠረው የስራ ዕድል በዓመቱ ከታቀደው 3 ሚሊዮን የስራ ዕድል ነው። ከተፈጠረው የስራ ዕድል 65 በመቶው ቋሚ፣ 35 በመቶው ደግሞ ጊዜያዊ እንደሆነና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን አውስተዋል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ ካለባት ድህነትና ስራ አጥነት አንጻር ሰፊ ስራ አንደሚጠይቅ ነው ያነሱት። በአሁኑ ወቅት ከዕቅዱ ግማሹን ማለትም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣት ስራ ማስያዝ ይጠበቅ እንደነበር ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በአጋርነት ከሚሰራባቸው አገራት 240 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ በማግኘት ራሱን አደራጅቷልም ብለዋል። የስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ በአንድ ተቋም የሚሰራ ሳይሆን የተለያዩ ተቋማት እገዛም ያስፈልገዋል ነው ያሉት። በአገሪቷ በሚፈጠሩ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችና ሃብቶች በርካታ የሰው ኃይል የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆንም ገልጸዋል።