ቀጥታ፡

አገረ መንግስቱን ማስቀጠል የሚችል ተቋም የመፍጠር ስራ ለውጡን ለሚመራው መንግስት ከፍተኛ ፈተና መሆኑ ተገለፀ

ጥር 25 ቀን 2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት አገረ መንግስቱን ለማስቀጠል ተቋማትን የመፍጠርና የመገንባት ስራው ላይ የሞት የሽርት ትግል እንደገጠመው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛዓመት የስራ ዘመን በ1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ አገሪቱ ከለውጡ በፊት እንደ አገር መቀጠል የማትችልበት ሁኔታ መፈጠሩንና በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ወደ ፊት መጓዝ ብቻ ሳይሆን ባለችበት ለመቀጠልም አዳጋች  ሁኔታ ገጥሟት እንደነበር አስታውሰዋል።

ለውጡ ሲጀመር አገረ መንግስቱ በግለሰቦች እጅ መያዙንና በጥቅም፣ በዘር፣ በጓደኝነት እና በቤተሰብ እስከ ታችኛው መዋቅር የተደራጀ ያልተገባ ትስስር እንደነበር ገልፀዋል።

ከለውጡ በኋላም ይሄንን ያልተገባ ትስስር ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ መንገድ ባለመኖሩ የለውጡን ፈተና ማብዛቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩ ችግሮች ምንጩ ገዢው ፓርቲ  በመሆኑ ይሄን ለማከም አዲሱን አስተሳሰብ መሸከም የሚችል ሰው ተኮር ፓርቲ መቋቋሙን ገልፀዋል።

በዚህም ከ35 ዓመታት በላይ አብረው ክፉና ደጉን ያዩ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ መለያየታቸውን አውስተዋል።

የፓርቲዎች መለያየት እንደ እስረኞች መፍታት ቀላል ያለመሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የከፋ አደጋና ግጭት ሳያመጣ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መከወን መቻሉንም ተናግረዋል።

ከፓርቲ ቀጥሎ አደገኛ ምሰሶ የሆኑትን እንደ የደህንነት፣ፖሊስና የመላከያ ሰራዊት ያሉ የጸጥታ ተቋማት ቀደም ሲል በነበረው ልምምድ ከአስፈፃሚው አካል እኩል ስልጣን እንደነበራቸው አንስተዋል።

እነዚህን ተቋማት በለውጥ ሂደት አልፈው እንዲቀየሩ በማድረግ በትክክል ስራቸውን እንዲሰሩ ለማስቻል ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ተቋማት በተወሰነ ደረጃ ለማስተካከል በሃላፊና በህግ ደረጃ ማሻሻያ ለማድረግ የለውጡ አመራር ችግር እንዳልነበረበት ገልፀዋል።

ከባለሙያ ጋር ተያይዞ  በዘርፉ የሚሰሩ የደህንነት ባለሙያዎች እንደሌላው መስክ ዝም ብሎ መቀያየር የማይቻል በመሆኑ እልህ አስጨራሽ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህ ምክንያት በአጭር ጊዜ መለወጥ የሚገባቸው የተቋም ግንባታ ስራዎች የከፋ አደጋ ሳያደርሱ ጥረት እየተደረገና ውጤትም እየተመዘገበ እንዳለ ተናግረዋል።

አገረ መንግስትን ማስቀጠል የሚችል ተቋም የመፍጠር ስራ ለውጡን እየመራ ላለው መንግስት ከፍተኛ ፈተና መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መላው ኢትዮጵያዊ ያለውን ፈተና ሊገነዘብው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሴራ ፖለቲካ በመላ አገሪቱ ያልተገባ ስርዓት አልበኝነት እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተሟላ ደረጃ ለማስቆምም ፈተና መሆኑን እንዲሁ ተናግረዋል።

ነገር ግን የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ እቅዶች በብቃት እንደተከወኑ ሁሉ ''የሴራ፣ የተንኮል ፣ የደባ እና የሽብር ፖለቲካን በማሸነፍ ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም