መንግስት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ በወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ከገጠመው ችግር ታድጎታል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ በወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ከገጠመው ችግር ታድጎታል
አዲስ አበባ ጥር 25/2012 (ኢዜአ) መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባደረገው ማሻሻያ በግንባታው አፈጻጸም ላይ ለውጥ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት የግድቡን ግንባታ የሲቪል ምህንድስና ስራን ለጣልያኑ የስራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፔርጂሎ፤ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ደግሞ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ተሰጥቶ እንደነበር አንስተዋል። የሲቪል ምህንድስና ስራው በተገቢው ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ግን መዘግየት እንደታየበት አብራርተዋል። ሜቴክ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ልምድ የሌለው በመሆኑ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ሳያጠናቅቅ በመቅረቱ የሳሊኒ ኩባንያ በደረሰበት የስራ መጓተት ከመንግስት 900 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ መጠየቁንም ገልጸዋል። ክፍያው ባለፉት ሦስት ዓመታት የሲቪል ምህንድስና ግንባታው ተጠናቆ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ሳይሰራ በመቆየቱ የተከሰተ የኪሳራ ጥያቄ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ''ሜቴክ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርቶ የማያውቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በግድቡ ግንባታ ማከናወን የሚገባውን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ሳያጠናቅቅ ቀርቷል'' ብለዋል። መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይ የተፈጠረውን ችግር በመረዳቱ በወሰደው የማሻሻያ ስራ በአሁኑ ወቅት ግንባታው በሚፈለገው መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት። መንግስት በግድቡ ላይ የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወሰደው እርምጃ በግድቡ ግንባታ ላይ አመርቂ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል። በሌላ በኩል መነሻውን ከህዳሴ ግድብ ያደረገው የሆለታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በአቅም ግዙፉ እንደሆነና ከተጠናቀቀ ሁለት ዓመት እንደሆነው ተናግረዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን መጠናቀቅ ተከትሎ ደረጃውን የጠበቀ ፈጣን የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁንም አክለዋል። ያም ሆኖ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ከግድቡ ጀምሮ የተዘረጉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥቅም ሳይሰጡ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸው ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 71 በመቶ የደረሰ ሲሆን በጣልያኑ የስራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፔርጂሎ የሚከናወነው የሲቪል ምህንድስና ስራ 86 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ደግሞ 35 በመቶ ደርሷል።