አንድ ክልል ብቻውን ተነጥሎ ከውጭ አገሮች ጋር የራሱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር አይችልም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
አንድ ክልል ብቻውን ተነጥሎ ከውጭ አገሮች ጋር የራሱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር አይችልም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ፣ጥር 25/2012 (ኢዜአ) አንድ ክልል ብቻውን ተነጥሎ ከውጭ አገሮች ጋር የራሱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሀመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚሁ መሰረት ክልሎች ከውጭ አገሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከውጭ አገራት ጋር ስለሚመሰረት የዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት የክልሎች ሳይሆን የፌዴራል መንግስት መሆኑን አስረድተዋል። ''አንድ ክልል ያለ ፌዴራል መንግስት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እውቅና ከሌሎች ሉአላዊ አገራት ጋር ግንኙነት መፍጠር አይችልም'' ብለዋል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ክልል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በሚደረግ ህጋዊ አካሄድ በመከተል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማካሄድ እንደሚችል ገልጸዋል።