ቀጥታ፡

በሴቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመከላከል የአፍሪካ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ጥር 25 ቀን 2012 (ኢዜአ) በጦርነትና ግጭት በሴቶች ላይ የሚደርስን የሞት ፣ የመደፈርና የአካላዊ ጉዳት ለመከላከል የአፍሪካ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አማካሪ አምባሳደር ኦስማን ኬህ ጠየቁ።

የአፍሪካ ህብረት "ስርአተ ጾታ የኔ አጀንዳ ነው ዘመቻ'' ቅድመ ምክክር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ምክክሩ ጦርነትንና ግጭትን በማስቆም የሴቶችን ውክልና ማስፋት ላይ ያተኮረ ነው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተያዘውን ጎርጎሮሳውያንን 2020 አመት ‘’ለአፍሪካ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጦር መሳሪያ ድምጽን ማጥፋት’’ ብሎ ሰይሞታል።

በዚህም በጦርነትና ግጭት ወቅት የሴቶችና ህጻናትን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ሰላም በማምጣት፣ ግጭትን በመፍታት የሴቶችን ሚና ማሳደግ የሚል ስምምነት ተደርጓል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አጀንዳ 2063 ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ማስቆም ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ሆኖም ሴቶችና ህጻናን ለሞት፣ ተገዶ መደፈር፣ ስደትና አካላዊ ጉዳት እየዳረጉ ያሉ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት አሁንም ለአፍሪካ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ተነስቷል።

በአለም እየተደረጉ ካሉ 34 ወታደራዊ ጦርነቶች 14ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ የ2019 የግጭት፣ የሰብአዊ መብትና ሰላም ግንባታ ሪፖርት ያመለክታል።

በዚሁ አመት 140 ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በሴቶችና ህጻናት ላይ መከሰታቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው አመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል።

በተመሳሳይ በአህጉሩ ያለው ግጭትና ጦርነት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለስደት፣ ከ15 ሚሊዮን በላይ ደግሞ ለውስጣዊ መፈናቀል ዳርጓል።

በዚህም ሴቶች ለሞት፣ መደፈርና ሌሎች አካላዊና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ መሆኑ ነው የተነሳው።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አማካሪ አምባሳደር ኦስማን ኬህ የአፍሪካ መሪዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል።

በ2063 የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ጦርነትና ግጭትን በመግታት የሴቶችን ውክልና መጨመር እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት።

በመሆኑም በ2020 ጦርነትን ለማቆም የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ እንደ አህጉር ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ቢሆንም አገሮች የራሳቸው እቅድ ማውጣት መስራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሳማታ በበኩላቸው አፍሪካ በግጭት ምክንያት እያጣች ካለው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ጦርነትና ግጭትን በማስቆም ለሴቶችና ህጻናት ምቹ የሆነች አፍሪካን መፍጠር እንዲሁም ውክልናቸውን መጨመር ለነገ የሚባል ተግባር እንዳልሆነ በአጽኖት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን በኢትዮጵያ አሁን ባለው ውስጣዊ ግጭት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሆኖም ሴቶች ሁልጊዜ እንደተጠቂ ብቻ ሳይሆን በሰላም ድርድር፣ በፖለቲካ ውሳኔ፣ የሴቶች ተሳትፎን ማሳደግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

"ስርአተ-ጾታ የኔ አጀንዳ ነው ዘመቻ" 55 የሲቪል ማህበር ተቋማትን ያካተተ ሲሆን የስርአተ ጾታ እኩልነትና የሴቶች መብትና የጾታ እኩልነት ላይ ትኩረት በማድረግ በጎርጎሮሳውያኑ 2002 የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም