ቀጥታ፡

የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ መንግስት በጥንቃቄ እየሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ ጥር 25/2012 (ኢዜአ) መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱና ወንድማማቾች ደም እንዳይቃቡ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው። የምክር ቤቱ አባላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ለሞትና ለእንግልት እየተዳረጉ፣ ዘረፋና ስርቆት እየተስፋፋ፣ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያውኩ በርካታ ህገ-ወጥ ተግባራትም እየተፈጸሙ መሆኑን አንስተዋል። ተማሪዎችን በማገት ገንዘብ የሚጠይቁና ይህ ሳይፈጸምላቸው ሲቀርም ህጻናትን ጭምር ለሞት የሚዳርጉ ሕገ-ወጦች እየተበራከቱ መጥተዋል ሲሉም ጠቁመዋል። እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን ያነሱት የምክር ቤት አባላቱ መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ምን እየሰራ ነው? ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምላሻቸው መንግስት ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ፣ በንግግርና በውይይት ለመፍታት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን የሴራ ፖለቲካ አራማጆች አሁን ያለውን መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት በሕዝቡ ይሁንታን እንዲያጣ እየጣሩ ነው፣ ዜጎችንም ለእንግልት እየዳረጉ ነው ብለዋል። በአንድ ወገን መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር አቅቶታል ለማስባል፤ በሌላ ወገን ደግሞ ሰዎችን እየገደለ ነው በሚል አበክረው የሚሰሩ ፖለቲከኞች አሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የምክር ቤቱ አባላትና ሕዝቡ መገንዘብ ያለበት ይህ የፖለቲካ አካሄድ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያፋጅ በመሆኑ በሰከነ መንፈስ በማየት ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ነው ብለዋል። ''ይህን የሴራ ፓለቲካ በማስቀረት ኢትዮጵያ እንደ አገር እንደምትቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ'' ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ። መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ንጹሃን ወገኖች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በጥንቃቄ እየሰራ ነው ሲሉም አክለዋል። 'መንግስት በአንድ አገር ሁለት የታጠቀ ኃይል እንዳይኖር ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው፤ በቀጣይም ይወስዳል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲከኞች ንጹሃን ዜጎችን ለፖለቲካ መሳሪያነት ከመጠቀም እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም