በፍርድ ቤቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት እውነተኛ ነፃነት ያስፈልጋቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፍርድ ቤቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት እውነተኛ ነፃነት ያስፈልጋቸዋል
አዲስ አበባ ጥር 25 /2012 (ኢዜአ) በፍርድ ቤቶች ላይ ተግባራዊ ለውጥ ለማምጣት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትና እውነተኛ ነፃነትን የሚተገብሩበት ህግ እንደሚያስፈልጋቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ተናገሩ።
በአዲስ መልክ እየተዘጋጀ ባለው የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበ የማብራሪያ ጥያቄ ፕሬዚዳንቷ ምላሽ ሰጥተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የፌዴራል ዳኞችን በሚመለከት የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች ደንብ ማውጣት እንዲችል ስልጣን ይሰጣል።
ረቂቁ ዳኞች እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ያለ መከሰስ መብት እንዲኖራቸውም የሚደነግግ ነው።
የፌዴራል ዳኛ ሆኖ ለመሾም ከአሁን በፊት ይጠየቅ የነበረው ዝቀተኛው እድሜ ከ25 ወደ 30 ዓመት እንዲያድግ፣ ጡረታ የመውጫ ጊዜ ደግሞ ከ60 ወደ 65 ዓመት ከፍ እንዲልም የሚፈቅድ ነው።
ይህም በዋናነት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኛ ሆኖ ለመሾም የሚያስፈልጉ ሌሎች መስፈርቶች እንዳሉ ሆነው የእድሜ ብስለት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የሚያሳይ መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አስረድተዋል።
ጡረታንም በተመለከተ አንድ ዳኛ እድሜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ሙያዊ ብስለቱ ስሚዳብር ከመደበኛው የጡረታ ጊዜ ከፍ ማለቱ የካበተ ልምድ ያላቸውን ዳኞች ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ የዳኛ እጥረት ሲያጋጥም ከአንድ ፍርድ ቤት ወደሌላ ፍርድ ቤት አንድን ዳኛ አዛውሮ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ይደነግጋል።
ይህ ከመጀመሪያ ፍርድ ቤት ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ዝቅና ከፍ አድርጎ ማዘዋወር እንዲቻልም የሚፈቅድ ነው።
ረቂቅ አዋጁ የዳኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም የአገሪቱን የኑሮ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በየጊዜው ሊሻሻል የሚችልበትን አማራጭም አስቀምጧል።
የህግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን ሲመረምር ያገኛቸውን የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳ ሲሆን ከህገ መንግስት ጋር የሚጋጩ ሃሳቦች በጥንቃቄ እንዲታዩና እንዲስተካከሉ አሳስቧል።
በተለይ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ደንብ የማውጣት ስልጣን ይኑረው ወይስ አይኑረው፣ የዳኞች ያለመከሰስ መብት ይፈቀድ አይፈቀድ የሚለው ክርክር ተካሂዷል።
ከዚህ በተጨማሪም በምክር ቤቱ የተሾመ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ካለምክር ቤቱ እውቅና ወደ ከፍተኛ ወይም ከከፍተኛ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማዘዋወር የመሳሰሉት የምክር ቤቱን ስልጣን የሚጋፉ መሆናቸው ተገልጾ ሰፊ ክርክር ተካሂዶባቸዋል።
ፕሬዚዳንቷ ወይዘሮ መዓዛ ''እነዚህ እይታዎች ከህግ አንፃር ልክ ቢሆኑም ነገር ግን ፍርድ ቤቶቹ ነፃ ሆነው የህዝብ አመኔታን እንዲያገኙና ከጫና እንዲወጡ ካስፈለገ ከተለመደው አሰራር መውጣት አለብን'' ሲሉ ተናግረዋል።
ካልሆነ ግን አሁንም ቢሆን ዳኝነቱን ከውስጣዊና ከውጫዊ ጫና ነፃ ለማድረግ ይህ አዋጅ በቂ ውይይትና መተማመን ላይ ተደርሶ መፅደቅና ተግባራዊ መሆን እንዳለበት በመግለጽ አስረድተዋል።