ቀጥታ፡

ባለሃብቶች በቆላ ስንዴ የመስኖ ልማት ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

ሰመራ ኢዜአ ጥር 25 ቀን 2012 በአዋሽ ተፋሰስ የቆላ ስንዴን በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ሰፊ እድል በመኖሩ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ ። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በዓመት በአማካይ 67 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ያስፈልጋታል ። ሆኖም ግን በአገር ውስጥ በዓመት የሚመረተው የስንዴ ምርት መጠን 50 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ሲሆን ቀሪው 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ እየገባ እንደሚሸፈን አስረድተዋል ። መንግስት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ መጠን በመስኖ ልማት እንዲሸፈን ከማድረግ ባሻገር ስንዴን ወደ ውጭ መላክ የሚቻልበትን እድል ለማመቻቸት የቆላ ስንዴ ልማት ፕሮጀክትን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልፀዋል ። የወረር ግብርና ምርምር ማእከል ለቆላ ስንዴ ልማት አገልግሎት የሚውሉ ሰባት የዳቦና አንድ የፓስታና ማካሮኒ ምርጥ ዝሪያዎች በምርምር አውጥቶ እንዲባዙ እያደረገ መሆኑን ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ። ጋምቦ ፣ ሉሲ ፣ ወረር ፣ ፈንታሌ አንድ ፣ ፈንታሌ ሁለት ፣ አሚባራ አንድና አሚባራ ሁለት የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ምርጥ የቆላ ስንዴ ዝሪያዎች ለቀጣዩ ዓመት በዘር መልክ ለማቅረብ በ3ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ እየተባዙ ነው ተብሏል ። የቆላ ስንዴ ዝርያዎቹ ከ80 እስከ 90 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚደርሱና በሔክታር እስከ 45 ኩንታል የሚደርስ ምርት የሚሰጡ ናቸው ። አሁን እየተባዛ ካለው ምርጥ ዘር 150 ሺህ ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣይ የቆላ ስንዴን ለማስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ዶክተር ማንደፍሮ ገልፀዋል ። በአካባቢው የጥጥ ልማት የሚካሔድበት 350 ሺህ ሔክታር መሬት ባለሃብቶች በመካናይዜሽን ተጠቅመው በማፈራረቅ የቆላ ስንዴ ቢያመርቱበት እራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን መጥቀም እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ። በምርምር ማእከሉ የስንዴ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደስታ ገብሬ አንዳሉት ከሆነ ስንዴ ከጥጥ ጋር ሲነፃፀር ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ ያነሰና ምርታማ በመሆኑ ባለሃብቶች በስፋት ቢሳተፉ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ሙያዊ ምክር ለግሰዋል ። አቶ አህመድ መሀመድ  በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ በወረር አካባቢ የባዳሃሞ ቀበሌ ነዋሪና ባለሀብት  ሲሆኑ በአካባቢው ስንዴ በመስኖ ሲለማ አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል ። በ2010 ዓም ከወረር ግብርና ምርምር ማእከል የማዳበሪያ ፣ የዘርና የባለሙያ እገዛ አግኝተው በ34 ሔክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ በማልማት በሔክታር በአማካይ 37 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችለዋል ። ባገኙት ውጤት በመነቃቃት  በ2011 ዓም  በ260 ሔክታር መሬት ላይ ያለሙትን የቆላ ስንዴ በአጭዶ መውቂያ ኮምባይነር በመሰብሰብ ጥሩ ምርት ማግኘታቸውን ገልፀዋል ። በ2006 ዓም በአንዲት አርብቶ አደር 3 ሔክታር መሬት ላይ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ አሁን በተለያዩ ተፋሰሶች በስፋት እየተካሔደ ሲሆን በአዋሽ ተፋሰስ ብቻ በዘንድሮው የበጋ ወራት 12 ሺህ 500 ሔክታር መሬት እየለማ ነው ተብሏል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም