ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተጠቃ ሰው የለም

አዲስ አበባ ጥር 25 ቀን 2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ያለመኖሩን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በኢትዮጵያ እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተጠቃ ሰው  ባይኖርም   በነበራቸው የጉዞ ሰነድ ሶስት ኢትዮጵያውያንና አንድ ቻይናዊ በበሽታው ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ አመልክቷል። ኢንስቲትዩቱ በቻይና ተከስቶ በተለያዩ አገሮች እየተሰራጨ ያለውን የኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እየተሰራ ያለውን የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በሚመለከት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው። ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያና በ27 የድንበር ኬላዎች ላይ በተጠናከረ ሁኔታ የምርመራ ማጣራት ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ስለመሆኑ ገልጸዋል። እስከ ትናንት ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም 47 ሺህ 162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ መደረጉን ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 695 የሚሆኑት ቫይረሱ ከታየባቸው አገሮች እንደሆነ ገልጸዋል። ከቻይና የሚመጡ ሁሉም ተጓዦች በኢትዮጵያ በሚቆዩበት ጊዜ አድራሻቸውንና የተለያዩ ሰነዶች በመያዝ እስከ 14 ቀናት ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም የበሽታውን ምልክት በሚያሳዩበት ጊዜም ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት እንደሚረዳም አክለዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን በበሽታው የተጠቃ አንድም ግለሰብ ያለመኖሩን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከጉዞ ሰነድ ጋር ተያይዞ አራት ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል። እነዚህ ከተጠረጠሩት አራት ግለሰቦች አንዱ ቻይናዊ ሲሆን ሶስቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ በአክሱምና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማከሚያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚላክ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አራቱ ተጠርጣሪዎች አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የመጡ የመተንፈሻ አካል ህመምና ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያሳዩ ሁለት ሰዎችና ከእነርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ሁለት ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡ ይታወሳል። የዓለም የጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ ግዛት የተከሰተ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል። ድርጅቱ በሪፖርቱ መሰረት በሽታው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ እስከ ትናንት ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ከ23 አገሮች 14 ሺህ 557 ታካሚዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አስታውቋል። እስከ ዛሬ ጥር 25 ቀን 2012 ዓም 17 ሺህ 373 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 362 ታካሚዎች ደግሞ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም