ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ በወጣ ህዝብ ላይ የደረሰውን ጥቃት የተለያዩ ተቋማት አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ በወጣ ህዝብ ላይ የደረሰውን ጥቃት የተለያዩ ተቋማት አወገዙ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ በወጣ ህዝብ ላይ የደረሰውን ጥቃት የተለያዩ ተቋማት አወገዙ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና ዕውቅና ለመስጠት ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን የሽብር ድርጊት ተቋማቱ አውግዘዋል። ተቋማቱ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡትን ለውጥ እንደሚያደንቁም ጠቁመዋል። ተቋማቱ ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎች ያደረሱትን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል። ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን፣ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ድርጊቱን አውግዘዋል። በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና ዕውቅና ለመስጠት ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ መገኘቱ የሚታወስ ነው። በምስጋናና ድጋፍ ሰልፉ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ150 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።