ቀጥታ፡

በእዕምሮ እድገት ውስንነት ስፖርት ተሳታፊዎች ላቅ ያለ ውጤት በማምጣታቸው ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ጥር 24/2012 በእዕምሮ እድገት ውስንነት ስፖርት ተሳትፈው ሜዳሊያ ያመጡ ስፖርተኞች ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ዲቦራ ፋውንዴሽን ሽልማት ተበረከተላቸው።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ስፖርተኞች በቂ ድጋፍ ይደረግ እንዳልነበር ተገልጿል።

ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በግብጽ ካይሮ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በአራት አትሌቶች ተወክላ 2 ወርቅ፣ 1 ብር እና 4 ነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

ኢትዮጵያን ወክለው ከቀረቡ ስፖርተኞች ቁጥር አንጻር ውጤቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

በመሆኑም የውድድሩ ተሳታፊ ስፖርተኞችና የቡድን መሪ ባመጡት ውጤት እንዲበረታቱና በቀጣይ ጠንክረው እንዲሰሩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዚሁ መሰረት የውድድሩ ተሳታፊ አራት ስፖርተኞችና አንድ የቡድኑ መሪ ተሸልመዋል።

ለስፖርተኞቹ ሽልማቱን ያበረከቱት የኢዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ዲቦራ ፋውንዴሽን ናቸው።

በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በኩል ለልዑካን ቡድኑ ከ5 ሺህ እስከ 17 ሺህ 500 ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል።

በቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የተመሰረተው 'ዲቦራ ፋውንዴሽን' ደግሞ ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

ከዲቦራ ፋውንዴሽን የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ 50 ሺህ፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ 40 ሺህ እንዲሁም የነሀስ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች ደግሞ 30 ሺህ ብር ገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

እንዲሁም ለአሰልጣኝና ቡድን መሪ ለእያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል ።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ባደረጉት ንግግር ''እስካሁን በበቂ ሁኔታ የእዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው አትሌቶች ድጋፍ ሲደረግ አልነበረም'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአሁን በኋላ አስፈላጊ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የቡድኑ አሰልጣኝ የሸዋጌጥ ንብረት የኦሎምፒክ ኮሚቴው የስፖርት ትጥቅ ለሟማላት ላደረገው ቀና ትብበር ምስጋና አቅርበዋል።

የስፖርተኞቹ ቤተሰቦች የኦሎምፒክ ኮሚቴውና ዲቦራ ፋውንዴሽን ስፖርቱን ለመደገፍና ለማበረታታት ላበረከቱት ሽልማት አመሰግነዋል።

በህብረተሰቡ ውስጥ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ስለ አዕምሮ እድገት ውስንነት ያለው የተዛባ ግንዛቤ እንዲስተካከል በተለያየ መንገድ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም