ቀጥታ፡

በደብረ ማርቆስና በሚዛን አማን ከተሞች የመጠጥ ውኃ ችግር አጋጥሟል

ደብረማርቆስ ሚዛን  (ኢዜአ) ጥር 24 ቀን 2012 ዓም የደብረ ማርቆስና የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት መማረራቸውን ገለፁ። አስተያየታቸውን የሰጡት የሁለቱም ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደ ገለፁት የመጠጥ ውኃ አቅርቦቱ በሳምንት አንድ ቀን እንኳን እንደማይደርሳቸው ተናግረዋል ። የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ይፍቱስራ አበበ እንደተናገሩት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱ በተደጋጋሚ ከአንድ ሳምንት በላይ ስለሚጠፋ የምንጭ ውሃ ቀድተው ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል። ለምግብ ዝግጅት የሚሆን ውሃ በጀሪካን 15 ብር ድረስ በመግዛት ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልፀው  የከተማ አስተዳደሩ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል ። የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ ስመኝ ተመስገን በበኩላቸው በአካባቢያቸው ቢያንስ ለ10 ቀናት አቅርቦቱ እንደሚቋረጥ ተናግረዋል። በዚህም ለምግብ ማብሰያ፣ ለንፅህና መጠበቂያ፣ ለመጠጥና መሰል እለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እንደገጠማቸው ገልፀዋል ። ከጡረታ ደመወዛቸው አንዱን ጀሪካን ውኃ ከ15 እስከ 20 ብር ድረስ ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውንና ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በደብረማርቆስ ከተማ የቀበሌ 05 ነዋሪ እማሆይ እቴማአንች ይፍሩ ናቸው ። የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ እስከዚያ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መልስ ችግሩ የተከሰተው ከመብራት ሃይል አቅርቦትና በመሰረተ ልማት ግንባታ ሒደት መስመሮች በተደጋጋሚ ጊዜ የመቆረጥ አደጋ ስለሚደርስባቸው ነው ብለዋል ። የሀይል መቆራረጥ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ኃይል ለማግኘት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ምሰሶ ተከላ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል ። የውኃ አቅርቦት አማራጭ ለማስፋት የሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ በመጠናቀቁ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል ። ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም በ22 ሚሊዮን ብር በጀት አምስት መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓዶች ተቆፍረው የሞተር መግጠም ስራ ብቻ እንደሚቀር አስረድተዋል ። በተመሳሳይ ሁኔታ በሚዛን አማን ከተማ አሳሳቢ የሆነ የውኃ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ገልፀዋል ። የከተማው ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በበኩሉ ነዋሪዎቹ ያነሱት ቅሬታ ተገቢ መሆኑን በመግለፅ ችግሩን ለመፍታት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የዕድገት ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ገብረጻድቅ እንዳሉት የውሀ ችግሩ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በየወሩ የቆጣሪ ከመክፈል ያለፈ የውሀ አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑንና በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ የሚያገኙት ውሀ በቂ ባለመሆኑ ንጽህናው ያልተጠበቀ የጉድጓድ ውሀ ለመጠጣት መገደዳቸውን ገልጸዋል። በተደጋጋሚ ቅሬታቸው እንዲፈታ ቢጠይቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን በመግለፅ  መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡ ነዋሪው የወራጅ ወንዝ በመጠቀም ለተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች እየተዳረገ መሆኑንም አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል ። የሕብረት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘማች አዲሱ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በሳምንት አንድ ጊዜ ይለቀቅ የነበረው የመጠጥ ውኃ አሁን በሁለት ሳምንታት ጭምር የማይመጣበት ወቅት መኖሩን አስረድተዋል ። አቅርቦቱ በመቋረጡ ምክንያት የታሸገ ውሃ ገዝተው ለመጠጣት መገደዳቸውንና አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ መዳረጋቸውንም ወይዘሮዋ በምሬት ገልጸዋል። ውሃ መሠረታዊ ፍላጎት በመሆኑ አፋጣኝ መፈትሔ እንዲሰጠውም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል ። የሚዛን አማን ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ሣምሶን ሙሉጌታ በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ያነሱት የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግር ተገቢ መሆኑን ገልጸው በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ። የውሃ አገልግሎቱ የተቋረጠው በውሃ ማስተላለፊያዎች ላይ ብልሽት በመከሰቱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሣምሶን በጊዚያዊነት ከክልል ውሃ ቢሮ በተገኘ ድጋፍ አነስተኛ የማስተላለፊያ ቱቦ ተዘርግቶ አገልግሎት መስጠት እንደ ጀመረ ተናግረዋል። ብልሽቱ የውሀ አቅርቦቱን በግማሽ የቀነሰው ሲሆን የውሃ ማስተላለፊያ መስመሩ ተቀይሮ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ በመሆኑ በቀጣይ ሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር አቶ ሣምሶን ገልፀዋል፡፡ የከተማው የውሀ አቅርቦት ከተማው ዕድገት ጋር አልተመጣጠነም ያሉት ስራ አስኪያጁ ከረጅም ጊዜ እቅድ አንፃር በ141 ሚሊዮን ብር ወጪ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ለማከናወን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል ። የማስፋፊያ ሥራው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን የከተማዋ ንጹህ የመጠጥ ውሀ ሽፋን አሁን ካለበት 47 ከመቶ ወደ 80 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከስራ አስኪያጁ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም