የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ ነው
ጎባ ፣ጥር 24/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚታየውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ገለጸ ፡፡ ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸውን እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የባሌ ዞን ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች ገለፀዋል ፡፡ ኢንተር ራይዙ የምርጥ ዘር እጥረትን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ በሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልፇል። በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጫላ አበባ እንደገለፀት ኢንተርፕራይዙ በዋናነት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ የሚታየውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለማቃለል ለመጪው የመኽር አዝመራ ወቅት የሚውል ከ250 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ምርጥ ዘር የማዘጋጀት ስራ እያከናወነ ይገኘል ብለዋል ፡፡ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተዘጋጁ ከሚገኙት ምርጥ ዝርያዎች መካከል የዋግ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡና ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት ተገኝተው በኢንተርፕራይዙ የተባዙ የስንዴ፣ ገብስና የባቄላ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ “ስርጭቱ እንደየወረዳዎቹ የስነምህዳር ሁኔታ አግሮ ዲለር በሚባሉ የኢንተርፕራይዙ ወኪሎች አማካይነት አርሶ አደሩ ከአካባቢው ሳይርቅ በቀበሌው እንዲያገኝ እየተደረገ ነው” ብለዋል ። ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ምርጥ ዘር ማባዘትና ማሰራጨት ብቻውን ግብ አለመሆኑን ጠቁመው በዘር ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሌሎች ተዛማጅ የተሻሻሉ አሰራሮች ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ እማወሯ ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ስልጠናው በምርጥ ዘር ምንነትና አጠቃቀም፣በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ፋይዳው፣በማሳ ዝግጅት፣በሰብል አሰባሰብና በበሽታ ልየታና የገበያ ትስስር ላይ ያተኮረ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በየወቅቱ በሚሰጠው የግንዛቤ ስልጠና ምርጥ ዘሮችን የሚጠቀሙ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው ከማደጉም በላይ ለምርጥ ዘር ያላቸው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመራ መምጣቱንም ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ በስልጠናው ተሳታፊ ከነበሩና የኢንተርፕራይዙን ምርጥ ዘር ከሚጠቀሙ ሴት አርሶ አደሮች መካካል ወይዘሮ ሸምሲ ኡመር በሰጡት አስተያየት ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸው እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት የአካባቢውን ዝርያ በመጠቀም ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው የስንዴ ምርት ከ20 ኩንታል ወደ 65 ኩንታል በማደጉ በአንድ የአዝመራ ወቅት እስከ 300 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ከኢንተርፕራይዙ የሚቀርብላቸውን ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የስልጠና ተሳታፊ ወይዘሮ ሩቂያ በከር ናቸው፡፡ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው በሔክታር የሚያገኙትን የስንዴ ምርት ከ20 ኩንታል ወደ 70 ኩንታል ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል ። ሌላዋ አርሶ አደር ወይዘሮ ክበባ ተካ በበኩላቸው የአካባቢ ዘር ይጠቀሙ በነበረበት ወቅት የሚያገኙት ምርት አነስተኛ በመሆኑ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ለማሟላት ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ ። ምርጥ ዘርን በመጠቀም ምርታማነታቸው በመጨመሩ በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከሳር ክዳን ቤት ወደ ቆርቆሮ በመለወጥ በህይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማየት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡ በኢንተርፕራይዙ የሚሰጠቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግብርና ለማካሄድና ለመምራት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በዞኑ የሚገኙ ሮቤና ሲናና እርሻዎችን ጨምሮ በምስራቅ አርሲ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሄራሮ፣ ሁንጤና ቢሊቶ ሲራሮ የሚባሉ14 ሺህ 679 ሄክታር የሚለሙ ማሳዎች ያስተዳድራል።