የውጭ ኩባንያዎቹ የግድቡን ስራ አሁን እያከናወኑበት ባለው አግባብና ፍጥነት መቀጠል አለባቸው -- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ኩባንያዎቹ የግድቡን ስራ አሁን እያከናወኑበት ባለው አግባብና ፍጥነት መቀጠል አለባቸው -- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
አዲስ አበባ ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ስራቸውን አሁን እያከናወኑበት ባለው አግባብና ፍጥነት መቀጠል እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ዛሬ የህዳሴ ግድብን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን የሲቪል ምህንድስና የኤሌክትሮና ሀይድሮ መካኒካል ስራዎችን ከሚያከናውኑ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ በነበረው አስተዳደር ብዙ ሃብት አጥታለች። ኢትዮጵያ ግድቡን ከሶስት ዓመት በፊት ብትጨርስ ኖሮ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ማዳን ትችል እንደነበረና ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ከፍተኛ የሀገር ሃብት እንደባከነ አውስተዋል። በግድቡ ደካማ የፕሮጀክት አስተዳደር ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ ሃብት ብቻ ሳይሆን ህዝቡ በግድቡ ግንባታ ላይ ያለውን እምነት ማጣቱን ተናግረዋል። አሁን ባለፈው ነገር መቆጨት አግባብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገን ታሳቢ በማድረግ የግድቡን ስራ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል። መንግስት በወሰዳቸው የማስተካካያ እርምጃዎች ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የግድቡ ግንባታ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህም አኳያ የግድቡን ግንባታ ስራ እያከናወኑ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች የግድቡን ስራ አሁን ባለበት ፍጥነትና አግባብ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። አንዱ በፍጥነት ስራውን እያከናወነ አንዱ መዘግየት እንደሌለበትና ኩባንያዎቹ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የግድቡን ግንባታ በሚፈልገው ጥራት በመስራት የሁላችንም ህልም እውን ለማድረግ ተግተን መስራት ይገባናል ብለዋል። መንግስት የውጭ ኩባንያዎቹ ለሚገጥማቸው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል። የህዳሴ ግድቡን የሲቪል ምህንድስና ስራ እያከናወነ የሚገኘው የሳሊኒ ኢምፔርጂሎ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔትሮ ሳሊኒ አሁን ባለው የፕሮጀከት አስተዳደር ለውጥ ደስተኛ መሆናችውንና ኩባንያው የያዘውን ስራ ለማጠናቀቅ በቁርጥኝነት ይሰራል ብለዋል። የፕሮጀክት አስተዳደሩ ላይ ማስተካከያ መደረጉ ስራዎች በተፋጠነ ሁኔታ እንዲካሄዱ እያደረገ ነውም ብለዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው በኤሌክትሮና ሀይድሮ መካኒካል ስራዎች በጥራት ጉድለት ሲከናወኑ እንደነበር አስታውሰዋል። የነዚህ ስራዎች መዘግየት የሲቪል ምህንድስና ስራውን አጓቶት ነበር ብለዋል። መንግስት በወሰደው ማሻሻያ በኤሌክትሮ ሃይድሮ መካኒካል ስራዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ታይቷል ብለዋል። የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች በመሆናቸው ተቀናጅቶ መስራት ትልቁ ፈተና እንደሆነና ይሄንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የስራዎችን ቅንጅትና ቅንብር የሚያስተባበር የፕሮጀክት ቡድን ተቋቋሟ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ኩባንያዎቹ ቀን ተቀን ውይይት እንደሚያደርጉ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡም ተናግረዋል። በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም አንዱ ሲሆኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከ50 ዓመት በኋላ እንደሆነ ይገልጻሉ። ዛሬ የተመለከቱት ነገር ውጭ ሆነው ስለ ግድቡ ከሚሰሙት ፍጹም የተለየና ባዩት ነገር በጣም መደነቃቸውን ተናግረዋል። በዛሬው ጉብኝት ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ከተጠቀመች ማደግ እንደምትችል መገንዘባቸውንና ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ መስራት አለበት ብለዋል። የሕዳሴው ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 71 በመቶ የደረሰ ሲሆን በጣልያኑ የስራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፔርጂሎ የሚከናወነው የሲቪል ምህንድስና ስራ 86 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ደግሞ 35 በመቶ ደርሷል።