በሕዳሴ ግድቡ የወሰድነው የሪፎርም እርምጃ ግድቡን ከገጠመው ችግር እንድንታደገው አድርጓል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድቡ የወሰድነው የሪፎርም እርምጃ ግድቡን ከገጠመው ችግር እንድንታደገው አድርጓል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በሕዳሴ ግድቡ የወሰድነው የሪፎርም እርምጃ ግድቡን ከገጠመው ችግር እንድንታደገው አድርጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ግድቡ የመደመር ፍልስፍና በአግባቡ ገቢራዊ ከሆነ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጎበኙበት ወቅት ነው። ከጉብኝታቸው ጎን ለጎንም የግድቡን የሃይድሮና ኤልክትሮ መካኒካልና የሲቪል ስራዎች ከሚሰሩ ኩባንያዎች አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። ዶክተር አብይ የግድቡ ግንባታ በመጓተቱ ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉም በላይ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ እንዳሳጣት ነው ያብራሩት። ይህ የሆነው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሃድሮና ኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን በአግባቡ መከወን ባለመቻሉ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በርካታ ወጪ ወጥቶባቸው ከግድቡ ጀምሮ የተዘረጉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥቅም ሳይሰጡ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል ብለዋል። ወጪው ሌሎች አትራፊ ፕሮጀክቶች ላይ ቢውል ያለውን መስመር መዘርጋት የሚችል ገቢ ያመጣ እንደነበር ጠቁመው፤ ይህ የአመራር ክፍተትን ያሳያል ነው ያሉት። ከአንድ ዓመት በፊት ግድቡን በጎበኙበት ወቅት ይህንና ሌሎች እንከኖችን በማየታቸው አዝነው እንደነበር አስታውሰው መንግስት ሳይውል ሳያድር ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል። የአመራር አካላትን መቀየርና የውጭ ኩባንያዎችን ወደ ስራው ማስገባት ደግሞ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በዛሬው ጉብኝታቸው የተወሰደው ሪፎርም ፍሬ እንዳፈራ መገንዘባቸውን በመግለጽ። ግድቡ የመደመርን መሰረታዊ ፍልስፍናዎች ገቢራዊ ማድረግ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ያሳየ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በግድቡ የተገኘው ውጤት ስህተትን ማረም፣ ጥንካሬን ማስቀጠልና ለመጪው ትውልድ ወረትን ማካበት እንደሚያስተምርም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። ይህን አሰራር በሌሎች ተቋማትም መድገም ከተቻለ የኢትዮጵያ ብልጽግና ቅርብ እንደሆነም አመላክተዋል። የሕዳሴው ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 71 በመቶ የደረሰ ሲሆን በጣልያኑ የስራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፔርጂሎ የሚከናወነው የሲቪል ምህንድስና ስራ 86 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ደግሞ 35 በመቶ ደርሷል።