የ "ዲስክ ጎልፍ " ውድድር በአሶሳ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የ "ዲስክ ጎልፍ " ውድድር በአሶሳ ተካሄደ
ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ "ኦፕን የዲስክ ጎልፍ " የተሰኘ ውድድር ዛሬ ተካሄደ። የዲስክ ጎልፍ ከአሜሪካ የጎልፍ ጨዋታ ጋር እንደሚመሳሰልና በሰፊ ሜዳ ላይ በመቶ ሜትር ርቀት የፕላስቲክ ዲስክ በመወርወር ከብረት ቅርጫት ውስጥ በማስገባት የሚሄድ ውድድር ነው። አንድ ውድድር ከሶስት እስከ አምስት ስፖርተኛች የሚያሳተፉ ሲሆን ዳኛ የለውም። ይህው ውድድር በኢትዮጵያ የተጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው። ዛሬ ውድድር አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ኢኖቨ ከተባለ ተቋምና አለም አቀፍ ዲስክ ጎልፍ ስፖርተኛችች ማህበር ጋር በመተባበር እንደተዘጋጀ በማህበሩ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ዮሐንስ ደሳለኝ ገልፀዋል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታ ከአሜሪካ ፣ ሳዑዲ እና ደቡብ አፍሪካ ፣ ከኢትዮጵያ ደግሞ ከወታደራዊ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 41 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግቢ በአራት ዙሮች ውድድሩ ተከናውኗል። ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ስፖርተኞች የወርቅ ፣የብር፣ የነሐስ ሜዳልያዎችን እንዲሁም የገንዘብ ሸልማት ተበርክቶላቸዋል።