ቀጥታ፡

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፕሪሚየር ሊጉን መምራት ጀምሯል

አዲስ አበባ  ጥር 23/2012 (ኢዜአ) ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የኢትዮጵያን እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መምራት ጀምሯል። የፕሪሚየር ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በቦንጋ ተካሂደዋል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፌዴራል ፖሊስን 34 ለ 22 አሸንፏል። ውጤቱን ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 10 በማሳደግ የሊጉን መሪነት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ተረክቧል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እስካሁን በሊጉ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች ያሸነፈ ሲሆን በአንጻሩ ፌዴራል ፖሊስ ከአምስት ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፎ አንዱን ብቻ ማሸነፍ ችሏል። ቦንጋ ላይ በተካሄደው የሊጉ ጨዋታም ከምባታ ዱራሜ ሚዛን አማን ከተማን 44 ለ 20 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። ከምባታ ዱራሜ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ በአንጻሩ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ በሊጉ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል። ሚዛን አማን ከተማ ቴፒ ላይ ጨዋታውን ማድረግ የነበረበት ቢሆንም የመጫወቻ ሜዳው ለውድድር የማይመጥን በመሆኑ ክለቡ በሁለተኛ አማራጭነት ባስመዘገበው የቦንጋ መምህራን ኮሌጅ ሜዳ ጨዋታውን እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ነገ በክልል ከተሞች ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚጫወቱ ሲሆን መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጨዋታውን ካሸነፈ መሪነቱን ዳግም ይረከባል። ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከጠዋቱ በ3 ሠዓት ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ10 ነጥብ ሲመራ፤ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ8   ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ6 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም