ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ ቢሾፍቱ ይካሄዳል

አዲስ አበባ  ጥር 23/2012 (ኢዜአ) 13ኛው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ በቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል። በግማሽ ማራቶን ውድድሩ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች የተውጣጡ 427 ወንድና 146 ሴት ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፤ ለአሸናፊዎችም የመቶ ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም በፖላንድ ዲንያ ከተማ በሚካሄደው 24ኛው የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ነው። በውድድሩ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተወዳዳሪዎች በፖላንዱ ውድድር እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። "የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለፖላንዱ ውድድር ከነተጠባባቂዎቹ ምን ያህል አትሌቶች ይመዝገቡ?" የሚለውን ጉዳይ እንደሚወስን አመልክተዋል። ከኮሚቴው ውሳኔ በኋላ የተመረጡት አትሌቶች ወደ ዝግጅት እንደሚገቡም ገልጸዋል። ለአትሌቶች የውድድር ዕድል ከመፍጠርና ከማበረታታት አንጻር የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ20 ሺህ፣ የ10 ሺህ እና የ7 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረከትና ለዚህም 100 ሺህ ብር እንደተዘጋጀ ጠቁመዋል። ነገ የሚካሄደውን 13ኛውን የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር የተመለከተ የቴክኒክ ስብስባ ዛሬ በቢሾፍቱ የባህል ማዕከል ተካሂዷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያና አቶ አስፋው ዳኜ ለክለብ፣ ለክልልና ከተማ አስተዳደር የአትሌቲክስ ቡድን መሪዎች ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም