ቀጥታ፡

የባቡር ትራንስፖርቱ ቀልጣፋ ባለመሆኑ የተገልጋዩን ችግር እያቃለለ አይደለም

አዲስ አበባ ( ኢዜአ ) ጥር 23/2012  የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ቀልጣፋነት የጎደለው በመሆኑ ችግራቸውን እየፈታላቸው አለመሆኑን ተጠቃሚዎች ተናገሩ። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። አገልግሎቱን የጀመረውም በ41 ባቡሮች ተሳፋሪዎችን በሁለት መስመሮች በማመላለስ ነው። አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 34 ቀላል ባቡሮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ በገጠማቸው ብልሽት ስራ ማቆማቸው ነው የተገለፀው። ከስራ ውጭ የሆኑትን ሰባት ባቡሮች ወደ ስራ ለማስገባትና ለህብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የመለዋወጫ እጥረት ማጋጠሙም ይነሳል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች እንደሚሉት የባቡር ትራንስፖርት የተገልጋዩን ችግር በተወሰነ መልኩ ቢያቃልልም ቀልጣፋ አይደለም። በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ሠዓት የተጠቃሚው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ መጉላላትና መጨናነቅ የተለመደ ነው። ወጣት ሚሊዮን ኃይሉ  " ባቡሩ በሚሄድበት ጊዜ አንዳንዴ ይቋረጣል፣ መንገድ ላይ ይቆማል እና እነዛ ችግሮች ቢፈቱ" ሲል ተናግሯል። ወጣት መዝገቡ አለማየሁ በበኩሉ ለኅብረተሰቡ  የባቡሮቹ አገልግሎት  በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ  ቢሆንም  በስራ መግቢያና መውጫ ሠዓት ላይ  የመዘግየት ችግሮች መኖራቸውን አንስቷል። ፈርማታዎች ላይ የባቡሮቹ የመድረሻ ጊዜ  ቀደም ሲል ከነበረው  መሻሻሉን የገለጹት አቶ ተፈራ ባቦቁ  አሁንም የበለጠ ቢሻሻል ጥሩ ነው ብለዋል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት በበኩሉ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በሙሉ አቅም እንዳይሰራ በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና በመሰረተ ልማቱ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ችግር እየሆኑብኝ ነው ይላል። የትራንስፖርት ማኔጅመንት ዲፓርትመንት ዳይሬክተሩ አቶ አክሊሉ ኢቢሶ እንደሚሉት ባቡሩ የሚሰራበት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ገመድ መበጣጠስና የኃይል መቆራረጥ ያጋጥማል። በሀዲዶች ላይ የሚደርሱ የመኪና አደጋዎችም ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋቶች ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ባቡር፣ እግረኞችና ተሽከርካሪዎች በአንድ ላይ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ለደህንነት ሲባል ፍጥነቱ እንዲቀንስ ይደረጋል ይላሉ አቶ አክሊሉ። የባቡር መለዋወጫ እቃዎችን በሚፈለገው ልክ በአገር ውስጥ ገበያ የማይገኙና ከውጭ አገር የሚመጡ መሆናቸው አገልግሎቱን በሙሉ አቅም ለመስጠት የሚገጥሙ ፈተናዎች ናቸው። መለዋወጫ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት መኖሩም የተበላሹ ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ስራ ማስገባት አላስቻለም እንደ እርሳቸው ገለጻ። በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ባቡሮችን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች አቅም አስጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ቀላል ባቡሮቹ በ39 ጣቢያዎች በሚሰጡት አገልግሎት በቀን እስከ 120 ሺህ ተጠቃሚዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ። ቀደም ሲል ባቡሮቹ በየ15 ደቂቃ ልዩነት ምልልስ ያደርጉ የነበረ ሲሆን ይህ ሠዓት ወደ 10 ደቂቃ እንዲወርድ መደረጉን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም