በበልጉ ወቅት በሀገሪቷ አብዛኛው አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በበልጉ ወቅት በሀገሪቷ አብዛኛው አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ተገለጸ
አዳማ (ኢዜአ) ጥር 23/2012 በዘንድሮ የበልግ ወቅት በሀገሪቷ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጄንሲ ገለጸ። ኤጄንሲው ባለፈው የበጋ ወቅት በተሰጠው ትንበያ ዙሪያና በበልግ ወቅት የአየር ጸባይ አዝማሚያ ዙሪያ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ መክሯል። በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት በቀጣይ የበልግ ወቅት የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ጨምሮ አብዛኛው የሀገሪቱ ቦታዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል። ከመጪው የካቲት አጋማሽ ጀምሮ በሚቀጥሉት አራት ወራት ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም የምስራቁ ክፍል ቆላማ ስፍራዎች ከበቂ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙም አስታውቀዋል። በተለይም የጉጂ፣ ቦረና፣ ቆላማ የባሌ ዞን ወረዳዎች፣ ሶማሌና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሰብልና ለመስኖ ልማት አመቺ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸውም አመልክተዋል። "በህንድና ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚፈጠረው ሙቀት በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከባለፉት ሶሰት ዓመታት የተለየ በቂ ዝናብ ሀገራችን ታገኛለች " ያሉት አቶ ፈጠነ፤ አፋር፣ ከፊል ትግራይና ምስራቅ አማራ ደግሞ ከመደበኛው በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የዘንድሮ የበልግ ወራት አየር ትንበያ እንደሚያሳየውም በሀገሪቱ የተሻለና ለአዝመራ አመቺ የሆነ የዝናብ ስርጭት ይኖራል። ከዚሁ በተጓዳኝም ሰፊ የዝናብ ስርጭት ባለባቸው ቦታዎች የወባ ወረርሽኝና አልፎ አልፎም ጎርፍ ሊኖር ስለሚችል ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጠቁመዋል። የበልግ ዝናብ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ አካባቢዎች ለሰብል ልማት፣ ለመስኖና ግጦሽ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑም አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ይህን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባውም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የበጋ ወቅት የአየር ሁኔታን አስመልክቶ የሰጠው ትንበያ በተጨባጭ መሬት ላይ የነበረውን እውነታ ያመላከተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ ናቸው። በዚህም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሰውን የመኽር አዝመራ እንዳያበላሽ ትክክለኛ የአየር ሁኔታ ትንበያን በመስጠት አርሶ አደሩን ከጉዳት መታደግ መቻሉንም አውስተዋል። የደረሰው ሰብል በህብረትና በዘመናዊ መሳሪያዎች በፍጥነት እንዲነሳ መረጃ በመስጠት ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት በመቀነስ ረገድም ኤጀንሲው ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል። ኤጄንሲው ትክክለኛ የአየር ሁኔታ ትንበያ እንዲያከናውንም በዘመናዊ መሳሪያዎች መደራጀቱ በዘርፉ እየተመዘገበ ላለው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አመልክተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው "በቀጣዩ የበልግ ወራትም ሊኖር የሚችለውን የዝናብ ሥርጭት አርሶ እና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻል አለበት" ብለዋል ።