ቀጥታ፡

የፍቼ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ልማት ለማምጣት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

ፍቼ/ኢዜአ/ ጥር 23/2ዐ12 በአካባቢያቸው መልካም አስተዳደር በማስፈን ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። "የፍቼ ከተማ አስተዳደርና የሕዝቡ የልማት ተሳትፎ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው ዛሬ ህዝባዊ ውይይት ተካሄዷል። ነዋሪዎቹ በወይይቱ ወቅት ሀብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር ከአስተዳደሩ ጋር  እንደሚሰሩም ተናግረዋል። በከተማዋ የቀበሌ አራት ነዋሪ አቶ ተፈሪ ዘለቀ  በከተማው የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚቃለሉት ሁሉም በግልና በጋራ  የድርሻውን በጐ አሻራ ሲያሳርፍ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይም ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት ማምጣት የሚቻለው ወጣቶች፣ ሴቶችና ጐልማሶች የድርሻቸውን መወጣት ብቻ ሳይሆን ህግና ስርዓትን በማክበሩና ማስከበሩም ላይ በንቃት  ሲንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል። የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ግርማ ከበደ በበኩላቸው የሚስተዋሉ "ችግሮች እንዲወገዱ ባለሀብቶች፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት ሲንቀሳቀሱና ህብረተሰቡንም በስፋት መሳተፍ ሲችሉ ነው "ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ህገወጥ የቤት ግንባታ፣ የመሬት ወረራና ሰላምን የማደፍረስ ተግባራትን መታገል የእያንዳንዱ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባና ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ። በከተማው በሆቴል ንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ አዳነ ታደሰም ባለሀብቶች በሚያከናውኗቸው  ስራዎች ህብረተሰቡን አለማሳተፋቸውና አስተዳደሩም ችግሮች ሳይባባሱ ለማቃለል የሚያደርገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑ  ለከተማው ባለሀብቶችና ነዋሪዎች ፈተና መሆኑን ተገልዋል። እነዚህን ችግሮች ለማስወገድም አስተዳደሩ አሳታፊ እቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ እንዳለበት ጠቁመው"  ከስራ ይልቅ የጠባቂነት  ስሜት የሚፈጥሩ ድርጊቶችን በለጋነታቸው ማስወገድ ይጠበቅበታል" ብለዋል። በእሳቸው በኩል የአስተዳደሩን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። የፍቼ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዝመራው አደሬ በበኩላቸው በከተማው መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ለዚህም የህብረተሰቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። "በተለይም የመንግስትን ገቢ በማሳደግ የከተማውን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የእያንዳንዱ ነዋሪ ተሳትፎ ወሳኝ ነው "ብለዋል። በመድረኩ የከተማው የድህነት ገፅታና መፍትሄው፣ የህሕዝብ ተሳትፎ በሚሉና በሌሎች ርዕሶች ዙሪያ  ውይይት ተደርጐባቸዋል። በሰላሌ ኦሮሞ የባህል ማዕከል በተካሄደው ውይይት ከ1 ሺህ 5ዐዐ የሚበልጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች፣ የቀበሌ አመራር አካላትና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም