የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ለማደርገው በረራ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረኩኝ ነው አለ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በሚያደርገው በረራ ለመንገደኞችም ሆነ ለሠራተኞቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርመራና ጥንቃቄ እንደሚያደርግ አስታወቀ። አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ የኮሮና ቫይረስ በሌለባቸው ቤጂንግ፣ ሻንጋይ፣ ጉዋንዡ፣ ቼንግዱ እና ሆንግ ኮንግ እንደቀድሞው መቀጠሉን ነው የገለጸው። የኮሮና ቫይረስ ባለባቸው ሁለት የቻይና ግዛቶች ማለትም ኹዋን እና ሆቤይ በረራ እንደማያደርግም አስታውቋል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚከናወነውን የመከላከል ስራን አስመልክተው በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። ትናንት ምሽት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የዓለም አቀፍ መንገደኞች መግቢያ እየተካሄደ ያለውን ክትትልና ቁጥጥርም ለጋዜጠኞች አሳይተዋል። አቶ ተወልደ በዚሁ ጊዜ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና መብረር አቁመዋል እየተባለ ስለሚነሳው መረጃ ምንነት አብራርተዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ስጋቱ ዓለም አቀፍ መሆኑን ማረጋገጡን፣ በረራም ሆነ ጉዞ አለመከልከሉንና ይልቁንም መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ዝርዝር ጉዳዮችን ማውጣቱን ገልጸው እነዚህን ጥንቃቄዎች ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ በረራ ያቆሙ አየር መንገዶች ሰለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ተወልደ አብዛኞቹ ታዋቂ አየር መንገዶች ግን በረራቸውን መቀጠላቸውን ተናግረዋል። የሲንጋፖር፣ የካትሄይ ፓስፊክ፣ የአውስትራሊያ፣ የታይላንድ፣ የኒውዚላንድ፣ የኢንዶኔዥያ፣ የኤምሬትና ኳታር አየር መንገዶች በረራ እንዳላቋረጡ ጠቅሰዋል። አንዳንድ አየር መንገዶች ወደ ቻይና በረራ አቋርጠናል ሲሉ የጊዜ ገደብ ማስቀመጣቸውንና ይህም የቻይና አዲስ ዓመት እየተከበረ በመሆኑ እንደሆነም ጠቁመዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ከበደ በበኩላቸው ከየትኛውም አገር የሚመጣ መንገደኛ ሲገባ ሶስት ቦታዎች ላይ ይፈተሻል ብለዋል። ከ38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሙቀት መጠን ያላቸውን ሰዎች የተገጠሙት መሳሪያዎች እንደሚለዩና ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሆነ ገልፀዋል። "ሁሉም ከቻይና የሚመጡትን ነው ክትትል ለማድረግ እየተሞከረ ነው ያለው። በተለይ ግን ጥብቅ ክትትል የሚደረገው ከሁቤይ ግዛት የሚመጡት የበለጠ ጠንከር ያለ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል። ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር እየሰራን ነው ያለነው ዋናው ቫይረሱ ራሱ ኖቬል የሚባለው ቫይረስ ምርመራ አድርገን የምናረጋግጠው ሬጀንት መሳሪያዎች አሉ ሬጀንቱ ስለሌለ እሱን የማስመጣት ስራ እየገፋንበት ነው። በአጭር ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አግኝተናል እነዚህ እየተሰሩ ነው።" ብለዋል ዶክተር ሊያ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት በቻይናዋ ኹዋን ከተማ የተሰራጨውን የኮሮና ቫይረስ "አጣዳፊ የዓለም የጤና ሥጋት ወይም ቀውስ" ሲል ያውጅ እንጂ አገራት ወደ ቻይና ጉዞ እንዳያደርጉ ምንም አይነት መመሪያ አልሰጠም። ያም ሆኖ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮና ማደጋስካር ወደ ቻይና በራራ እንደማያደርጉ አስታውቀዋል። ገዳዩ ቫይረስ ከቻይና በተጨማሪ በ20 የዓለም አገራት ውስጥ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ተገኝቷል። በዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም የሚመራው የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ በተለይ ደካማ የጤና መሠረተ ልማት ባላቸው አገራት ሊፈጥር የሚችለው የጤና ቀውስ አሳሳቢ ስለ መሆኑ መግለፁ ይታወቃል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም