የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበርን የፈረስ ትርኢት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበርን የፈረስ ትርኢት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት ተጀምሯል
አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ጥር 23/2012 የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር የፈረስ ትርኢት በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የዝግጅት ስራ ላይ መሆኑን የአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ። የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር የተመሰረተበት 80ኛ ዓመት ዛሬ በአዊ ብሔረሰብ ዞን እንጅባራ እየተከበረ ነው። ፈረስ ከአዊ ማህበረሰብ ጋር የተቆራኘ ነው፤ አዊዎች ፈረስ ከበቅሎ፣ ፈረስ ከፈረስ እና ፈረስ መውለድ ካቆመች /ከመሰነች/ ላም ጋር በማጣመር ለእርሻ አገልግሎት እንደሚጠቀሙበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ማህበረሰቡ ፈረስን ለሰውና ለዕቃ ማጓጓዣ፣ ለሰረገላና ጋሪ መጎተቻ እንዲሁም በታሪክ ድርሳናት እንደተጠቀሰው በጦርነት ወቅትም መጠቀሙ ይወሳል። በሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ /ከ1928-1933 ዓ.ም/ ኢትዮጵያ ድል ስታደርግ የአዊ ማህበረሰብ ከሌሎች የኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በፈረስ በመዝመት ትልቅ ተጋድሎ እንደፈጸሙም ይነገራል። የአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ አዳል የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር አመሰራረት ከኢጣሊያ ሁለተኛ ወረራ ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳለው ይገልጻሉ። በጦርነቱ የተሰዉ የአዊና ሌሎች አርበኞችን ለማስታወስና በጠላት ወረራ ጊዜ ጠላት ድል የተደረገው በፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትና በፈረሰኛ ጦረኞች በመሆኑ ማህበሩ ጥር 23 ቀን 1933 ዓ.ም ተቋቋመ። ፈረስ ባላቸው 30 ሰዎች የተመሰረተው ማህበር አሁን ላይ ከ48 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ጠቅሰዋል። ከማህበሩ ምስረታ ጀምሮ በየዓመቱ የፈረስ ጉግስ፣ የፈረስ ሸርጥና ዳንግላሳ በሚባል ፈረስ የሚደረግ የፈረስ ግልቢያ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የፈረስ ግልቢያ ትርኢቱን ወንድም ሴትም ፈረሰኞች የሚያሳዩ ሲሆን የጋላቢዎቹ ባህላዊ አልባሳትና የፈረስ ጌጣጌጦች ለትርኢቱ ድምቀት ይሰጡታል። በአዊ ዞን የዘመናት ባህልና ትውፊት የሆነውንና ማህበሩ የሚያዘጋጀውን የፈረስ ትርኢት የማስተዋወቅ ስራ በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እየተከናወኑ ስለመሆኑም አቶ መለሰ ገልጸዋል። የፈረስ ትርኢቱን ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ በእንጅባራ ከመከበሩ በፊት በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተው የፈረስ ትርኢት እንደሚቀርብ ነው የተናገሩት። ይህን የፈረስ ትርዒት በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይስንና ባህል ተቋም/ዩኔስኮ/ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያስችል ስራም ላለፉት ሶስት ዓመታት እየተከናወነ ነው ብለዋል። የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጥናቶች እንዲካሄዱ በማድረግና የትውውቅ መድረኮችን በማዘጋጀት የትርዒቱን ባህላዊና ታሪካዊ ዳራ አስመልክቶ መረጃ እየሰበሰበ ነው ብለዋል። መምሪያው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ትርኢቱ በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ እየተደረገ እንደሆነም ነው አቶ መለሰ ያብራሩት። መረጃ የማሰባሰቡ ስራ ቀጣይነት እንደሚኖረውና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል። ባህሉን ይበልጥ ማስተዋወቅ ይቻል ዘንድ የመገናኛ ብዙሃን ፎረም መቋቋሙን፣ የአዊን ማህበረሰብ ቱባ ባህልና ትውፊት ለትውልድ የማስተላለፉ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። በዛሬው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ምስረታ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሁለት ሺህ ፈረሰኞች በእንጅባራ ስታዲየም ትርዒት እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል። ከፈረስ ትርዒቱ ጎን ለጎን የአዊ ማህበረሰብ የአለባበስ፣ የባህላዊ ምግቦችና መጠጦችና ሌሎች ባህሎችን የሚያስተዋወቅ አውደ ርዕይ ይካሄዳል። ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ትናንት በተካሄደ አውደ ጥናትም ጥናታዊ ጽሁፎች መቅረባቸውን አስታውሰዋል።