የእንቦጭ አረም ከአባያ ሀይቅ ወደ ጫሞ ሀይቅ በመስፋፋቱ አሳሰቢ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
የእንቦጭ አረም ከአባያ ሀይቅ ወደ ጫሞ ሀይቅ በመስፋፋቱ አሳሰቢ ሆኗል
አርባምንጭ ኢዜአ ጥር 23/ 2012፡- በጋሞ ዞን በአባያ ሀይቅ ላይ ተከስቶ የነበረው የእንቦጭ አረም ወደ ጫሞ ሀይቅ በመስፋፋቱ አሳሰቢ ደረጃ መድረሱን የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ጋንቡራ ጋንታ ለኢዜአ እንዳሉት በጫሞ ሀይቅ ላይ ከ10 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የውሃው ክፍል በአረሙ ተወሯል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በአባያ ሀይቅ ላይ ከ2ሺህ ሄካታር በላይ የሸፈነው የእንቦጭ አረም በሚፈጠረው ማዕበልና ከኩልፎ ወንዝ ተፋሰስ በመታገዝ ተስፋፍቶ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል። በተለይ አባያ ሀይቅ አዞዎች፣ ዘንዶና ጉማሬዎች የሚገኙ በመሆኑ በሰው ጉልበት ለማስወገድ አስቸጋሪ ቢሆንም ባለፈው ዓመት ህብረተሰቡ ባደረገው ጥረት ከተወረረው ውስጥ ከአንድ መቶ ሄክታር በላይ አረም ማስወገድ ተችሏል፡፡ በዚህም ስራ የጋሞ ዞንና አርባ ምንጭ ከተማ የመንግስት ሠራተኞች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዙሪያ እና ምዕራብ አባያ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ከ53 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ የአረሙ መከሰትና መስፋፋት ስርዓተ ምህዳሩን በማናጋቱ በሀይቆቹ ውስጥና ውጭ የሚገኙ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ቡድን መሪው ተናግረዋል። ሆኖም አረሙ በተወገደባቸው ስፍራዎች የጠፉ የግጦሽ ሣሮች እያገገሙ መሆናቸውን አመልክተው ከተያዘው ወር መገባደጃ ጀምሮ ከሀይቆቹ ሁለት መቶ ሄክታር እንቦጭ አረም ለማስወገድ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡ የእንቦጭ አረምን በዘላቂነት ለማስወገድ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተካሄደ ያለው ጥናት እስኪጠናቀቅ በአማራጭነት የሰው ኃይል በመጠቀም ለመከላከል ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል። በምዕራብ ዓባያ ወረዳ የነጭ ዓባይ ዓሣ አስጋሪዎች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ተስፋዬ ዳታ በበኩሉ በማዕበል ምክንያት የዓባያ ሀይቅ ዳርቻዎች በእንቦጭ አረም መወረሩን ተናግሯል። አረሙን ለመከላከልም በየዓመቱ በሚደረገው ዘመቻ የማህበሩ አባላት ከህብረተሰቡ ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጿል። በአሁኑ ወቅት አረሙ በሀይቁ ላይ በመስፋፋቱ ዓሳዎቹ መንቀሳቀስ እየተሳናቸው ለአደጋ መጋለጣቸውንም ጠቁሟል። የጣና ሀይቅን ጨምሮ የእንቦጭ አረም ከታየባቸው ሀይቆችና ወንዞች መካከል አባያ ሐይቅ፣ ዝዋይ ሐይቅ፣ የቆቃ ግድብና የባሮ ወንዝ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መነሻው ላቲን አሜሪካ እንደሆነ የሚነገረው የእንቦጭ አረም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1956 ዓ.ም አቡነ ሳሙኤል ግድብ መታየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።