አገራቱ በድርቅና በወንዝ ፍሰት ወቅት የሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ስርዓት ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
አገራቱ በድርቅና በወንዝ ፍሰት ወቅት የሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ስርዓት ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በድርቅና በወንዝ ፍሰት ወቅት የሕዳሴ ግድቡ በሚኖረው የውሃ አሞላል ስርዓትና የስራ ክንዋኔ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተገለጸ። በግድቡ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ ረቂቅ ሰነድ እንደሚዘጋጅም ከውይይቱ በኋላ የወጣው የኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ አሜሪካና የዓለም ባንክ የጋራ የአቋም መግለጫ አመልክቷል። የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ልዑካን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ ከጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ትናንት ተጠናቋል። የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሙያዎች በድርድሩ የተሳተፉ ሲሆን የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊና የዓለም ባንክ ተወካዮች ታዛቢዎች ነበሩ። ሶስቱ አገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ደረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ ውሃ በሚሞላበት የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል። በድርቅ፣ በተራዘመ ዓመታት ድርቅና በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት ወቅት የሚኖረው የግድቡ ውሃ አሞላል ተጽዕኖ እንዳያሳድርም እንዲሁም። በድርቅ፣ በተራዘመ ዓመታት ድርቅ፣ በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት ወቅት በየዓመቱና በረጅም ጊዜ የህዳሴ ግድቡ ስራ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያደርግ የአደጋ ቅነሳ ስርዓት ለመዘርጋትም ተስማምተዋል። ሶስቱ አገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመደበኛ የስነ ውሃ ሁኔታዎች በየዓመቱና በረጅም ጊዜ ስለሚኖረው የስራ ተግባር፣ የትብብር ስርዓት መዘርጋትና በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችና የመረጃ ልውውጥን በተመለከተ የህግ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት መወያየታቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው በአቋም መግለጫው ተመልክቷል። የግድቡን ደህንነት መጠበቅና ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን በማስመልከት ተጀምረው ያልተቋጩ ጥናቶችን መቀጠል በሚቻልበት ሁኔታም ላይ ተስማምተዋል። የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አገራቱ ስምምነት የደረሱባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የቴክኒክና የህግ ቡድኖቻቸውን የመጨረሻ ስምምነት እንዲያዘጋጁ መመሪያ መስጠታቸውንና ስምምነቱ እ.አ.አ በየካቲት 2020 ማብቂያ እንደሚፈረም የጋራ የአቋም መግለጫው አመልክቷል። ሚኒስትሮቹ ስምምነቱ በቀጠናው ስለሚያስገኘው የጎላ አስተዋጽኦና የሕዳሴ ግድቡ ስራና ክንዋኔ ለድንበር ተሻጋሪ ትብብር፣ ለቀጣናው ልማትና ኢኮኖሚ ትስስር ስላለው ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም በአባይ ወንዝ ልማት ያለው የድንበር ተሻጋሪ ትብብር የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል ያለው ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሮቹ ዳግም ማረጋገጣቸውን መግለጫው ያትታል።